የሸኔ የሽብር ቡድን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠላት በመሆኑ አምርረን ልንታገለው ይገባል

237

በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ አገራት ነፍጥ አንግበው ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች በሰላም ወደ አገር ቤት መመለሳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

በዚህም በርካቶች ህጋዊ እውቅና አግኝተው በቅርቡ በተካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የተሳተፉ ሲሆን ጥቂቶቹ ግን “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ በሰላም ወደ አገር ቤት ከገቡ በኋላ ነፍጥ አንስተው ህዝብን ለሰቆቃ እየዳረጉ ነው፡፡

ከእነዚህ ኃይሎች መካከል ከምስረታው ጀምሮ በንጽሃን ደም እጁ የተጨማለቀ አረመኔያዊ ደርጅት የሸኔ የሽብር ቡድን ዋነኛው ነው፡፡

ቡድኑ በስም እታገልለታለሁ ለሚለው የኦሮሞ ህዝብ እንኳ የማይራራና በግብሩም የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት በንጹሃን ላይ በሚፈጽማቸው ግፎች አረጋግጧል፡፡፡

ከሰሞኑም የሽብር ቡድኑ ዋና መሪ የሆነው ጃል መሮ (ኩምሳ ድሪባ) እና ምክትል መሪው ጃል ሰኚ (ያዴሳ ነጋሳ) ያደረጉት ምስጢራዊ የስልክ ልውውጥ ይህንኑ የቡድኑን እኩይ ዓላማ ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።

ምስጢራዊው የስልክ ልውውጡም የአሸባሪው ሸኔ መሪዎች ከጥፋት ውጪ ዓላማ የሌላቸው፤ እርስ በርስ የማይግባቡና የዘረፋ መስመራቸውን ብቻ ተከትለው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው  በግልጽ ያመላከተ ሆኗል፡፡

ቡድኑ አንዱ ሌላውን በማይሰማበትና በማያከብርበት በተበጣጠሰ የእዝ ሰንሰለት ላይ እንደሚገኝም እንዲሁ፡፡

ይህም ቡድኑ በኦሮሞ ህዝብ ስም ከመነገድ በቀር  ለሽፍትነት በማይመጥን ስብስብ የተሞላ ስለመሆኑ በግልጽ ያመላክታል፡፡

ሌላው ቢቀር በቡድኑ መሪዎች አንዱ የሌላኛውን የስልክ ጥሪ በማያነሳበት ተራ የመናናቅ መስተጋብር ውስጥ እንደሚገኙ ምስጢራዊው የስልክ ልውውጥ ያጋለጠ ሲሆን፤ ይህም የቡድኑን ዓላማ ቢስ ሩጫ ያሳያል፡፡

ሌላው ጉዳይ ቡድኑ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና ሰቆቃ እጅግ አሰቃቂ መሆኑ ነው፡፡

የቡድኑ ታጣቂዎች ለኦሮሞ ህዝብ የማይራሩና የኦሮሞ እናቶችን ጨምሮ ሴቶችን በመድፈርና በዘረፋ ላይ ተጠምደው የሚውሉ መሆኑን የቡድኑ መሪዎች በድምጻቸው አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም በውጭ አገራትና በአገር ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች “እውነት ከኦሮሞ እናት ነው የተወለዳችሁ?” እስኪሉ በቡድኑ ስራ እጅግ መማረራቸውን ነው ምስጢራዊው የስልክ ልውውጥ ያጋለጠው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነት እታገላለሁ ሲል የተደራጀው ይህ የሽብር ቡድን ሞፈርን ከመሬት አዋደው የሚኖሩ አርሶአደሮችን ከነህይወታቸው በማቃጠል የተፈጠረበትን የጥፋት  ምግባር  አሳይቷል፡፡

ይህም “ከህዝብ የተጣላ እድሜው አጭር ነው” እንዲሉ የቡድኑ ሞት ቅርብ መሆኑን ያመላከተ ነው፡፡

ሁለቱ የሽብር ቡድኑ መሪዎች ባደረጉት ምስጢራዊ የስልክ ልውውጥ፤ የመንግስት ሰራዊት የኦሮሞ ህዝብን ክብር ሰጥቶ እያገለገለ ሲሆን፤ በአንጻሩ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ከሽፍታ ባነሰ ስነ-ምግባር የኦሮሞ ህዝብን እያጎሳቆሉት ስለመሆኑ ያነሳሉ።

ይህም ቡድኑ የኦሮሞ ህዝብን ጥያቄ መመለስ ቀርቶ ማሰብ በማይችሉ ተራ የወንበዴዎች ስብስብ የተሞላ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡

ቡድኑ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለው ዘረፋ፣ ግድያና ሰቆቃ የቡድኑ መሪዎችን ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዲገኙ አድርጓል፡፡

ለዚህም ነው በስልክ ልውውጡ ላይ  “እኔ አልመራም፤ ተጠያቂ መሆንም አልፈልግም፤ ወደ ኋላ ተመልሰን ማስተካከል አለብን” ሲሉ የተደመጡት።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቡድኑ ታጣቂ መሪዎች ሃሳብና አካሄድ አቅጣጫ የሌለው ሲሆን፤ በቀጣይ እጣ ፈንታቸው ላይም ግራ ተጋብተዋል።

አንደኛው ሌላኛውን ማመን እንዳቃተውና እርስ በርስ እንኳ “ጠላት” ተብለው እንደሚፈራረጁ ምስጢራዊው የስልክ ንግግር አጋልጧል፡፡

ይህም 'ሌባ ሲሰርቅ እንጂ ... ' እንዲሉ የቡድኑ አመራር ነኝ ባዮች እርስ በርስ ተበላልተው የማለቃቸውን አይቀሬነት ያሳያል፡፡

በአጠቃላይ የሽብር ቡድኑ የሚፈጽማቸው ግፎች የሰው ልጅ ሁሉ ጠላት መሆኑን በግልጽ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከዚህ ቀደም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው እንዳሉት፤ አሸባሪው ሸኔ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠላት ነው፡፡

ቡድኑ እያዋረደና እየገደለ ያለው ዘር ቀለም ሳይል ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሲሆን፤ በዚህም ሁሉም ዜጋ ይህንን እኩይ ቡድን አምርሮ በመታገል እስከመጨረሻው ሊያጠፋው መነሳት አለበት ነው ያሉት፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የሸኔ የሽብር ቡድንን በቁርጠኝነት እየታገለ መሆኑን በመጥቀስ፡፡ 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም