የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡን በማስተባበር ለአቅመ ደካሞች የበዓል መዋያ ስጦታ አበረከተ

165

አርባ ምንጭ ፤ ሚያዚያ 14/2014 (ኢዜአ) የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡን በማስተባበር ባሰባሰበው ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የበዓል መዋያ ስጦታ ለ350 አቅመ ደካሞች ዛሬ አበረከተ፡፡

ለአቅመ ደካሞቹ  ከተበረከተው ስጦታ ውስጥ ዶሮ፣ ዘይት፣እንቁላልና ሽንኩርት ይገኙበታል።

ስጦታው በተበረከተበት ወቅት የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ማርቆስ ማቴዎስ ባስተላለፉት መልዕክት ፤ ክርስቶስ መስቀል ላይ የተሰቀለው ለመላው የሰው ልጆች ደህንነት ቤዛ መሆኑን ማወቅ ይገባናል ብለዋል፡፡

የትንሳኤን በዓል ስናከብር ለሌሎች ካለን በማካፈልና በመልካም ተግባራችን መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዛሬ  ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በማድረግ ለ350 ችግረኞች የበዓል መዋያ መበርከቱን የጠቀሱት ከንቲባው፤ ይህም ባለፉት ሶስት ቀናት የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማስተባበር የተሰበሰበ መሆኑን አስታውቀዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ፍቅሬ ለማ በሰጡት አስተያየት፤ከዓመታት በፊት የትዳር አጋራቸውን በሞት በማጣታቸው ሁለት ልጆቻቸውን ለብቻ ማሳደግ ከባድ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር  ያልጠበቅኩትን ድጋፍ በማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር እኩል በዓሉን እንዳከብር በማስቻሉ ደስታዬ ወደር የለውም ” ብለዋል፡፡

አቅመ ደካማና ደጋፊ የሌላቸው በመሆኑ ለትንሳዔ  በዓል ምንም የተለየ ዝግጅት እንዳልነበራቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላው ድጋፉ የተደረገላቸው የአካል ጉዳተኛ  ዲፊኔ ዲማ በተደረገላቸው ድጋፍ የከተማ አስተዳደሩን አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም