የትንሳኤ በዓልን ትህትናንና መልካም ነገሮችን በመፈጸም ማክበር ይገባል-- የሃይማኖት አባቶች

190

ሚዛን፣ ሚያዝያ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የትንሳኤ በዓል ትህትናንና መልካም ነገሮችን በመተግበር ማክበር ይገባል ሲሉ የሃይማኖት አባቶች አስገነዘቡ።

ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን ትህትና በተግባር መኖር ሥጋዊና መንፈሳዊ ፋይዳ አለው ሲሉ የሃይማኖት አባቶቹ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሸካ፣ ቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ ሀገረ ስብከት የትምህርትና ስልጠና ክፍል ኃላፊ ሊቀ ጠበብት ቀለመወርቅ አጥናፉ ትህትና ሰዎች በፍቅርና መተሳሰብ እንዲኖሩ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

"ኢየሱስ ክርስቶስ አምላካቸው ሆኖ ሳለ እንደ አገልጋይ የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ ስለ ፍቅር ዝቅ ማለትን አስተምሯል" ብለዋል።

ሰውን መውደድ ራስን የተሻለና ከፍ አድርጎ በማየት ሳይሆን ዝቅ ብሎ በመጠየቅና አንተ ትሻላለህ አንቺ ትችይለሽ በማለት የሚገለፅ አንደሆነ አስረድተዋል።

ከክርስቶስ የተማርነውን ትህትና እኛ ታላቆቻችንን በማክበርና በመደማመጥ "የሳሳውን ፍቅር በትህትና መጠገን አለብን" ብለዋል።

"በምድር  ላይ  ስንኖር ለሌሎች መልካም ማድረግን መለማመድ አለብን ያሉት ደግሞ የቤንች ሸኮ ዞን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ጴጥሮስ አበበ ናቸው።

"ክርስትና የምንናገረውን በተግባር የሚንኖርበት መሆን አለበት" ያሉት አስተዳዳሪው አስተማሪያችን ክርስቶስ አድርጎ ያሳየንን መልካም ነገር በማድረግ የምድርንና የሰማይ በረከት ማግኘት አለብን" ብለዋል።

ጥላቻን ለማስወገድ ክርስቶስ የከፈለውን ዋጋ በማሰብ በጾም የቆየ ክርስቲያን በሁልጊዜ ምድር ላይ የፍቅርና የሰላም ሰው ሊሆን ይገባዋል ሲሉም አስገንዝበዋል።

ትሁት ሰው የማያሸንፈው ነገር ባለመኖሩ ትህትና፣ መከባበርና መተሳሰብን እንደሚያጎለብት ነው ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከገለጹት ምዕመናን መካከል ደግሞ ወይዘሮ ገነት ማሞ "ክርስቶስ ስለእኛ የተቀበለውን መከራ እያሰብን ትንሳኤውን ስናከብር ከትህትና ጋር መሆን አለበት" ብለዋል።

የእርስ በርስ መተሳሰብና ፍቅርን ማጎልበት ጥላቻና ግጭትን በማስቀረት የአብሮነትና የመተሳሰብን ባህል እንዲጎለብት ያደርገዋል ሲሉም ነው የገለጹት።

የትንሳኤ በዓልን አቅመ የሌላቸውን ወገኖችን ቤቱ ያፈራውን በማካፈልና በመጠየቅ እንደሚያሳልፍ  ወጣት ሺህበላይ እምቶ ገልጿል።

የክርስቶስን መከራ መቀበል ስናስብ በሌሎች ላይ ክፉ ማሰብን በመጸየፍና መልካም በማድረግ ሊሆን ይገባል ብሏል።

"በጸሎተ ሐሙስ የተፈጸመውን የትህትና ጥግ በዘውትር ህይወታችን ብንተገብር ለራሳችንና ለሀገራችን ትልቅ ፋይዳ አለው" አለው ሲልም ነው የገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም