የሞዴል ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ባዛርና ኤግዚቢሽን ምርትን ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ የልምድ ልውውጥ እየተደረገበት ነው

98

ሚያዝያ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ያለው አገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ባዛርና ኤግዚቢሽን ምርትን ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ የልምድ ልውውጥ የተደረገበት መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።

የኤግዚቢሽን እና ባዛሩ ያለፉት አምስት ቀናት ቆይታን በተመለከተ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከተሳታፊ ኢንተርፕራይዞች ጋር ገምግሟል።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን፤  የሞዴል ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽን እና ባዛር ምርትን ለገበያ ከማቅረብ ያለፈ ጠቀሜታ የነበረው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ  ከመንግስት በተደረገላቸው ድጋፍ ምርቶቻቸውን ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ ለማስተዋወቅና እርስበርስ የልምድ ልውውጥ በማድረግ መልካም አጋጣሚ የፈጠሩበት እንደነበር አንስተዋል።

በኤግዚቢሽን እና ባዛሩ ላይ  የታዩ ደካማ ጎኖችን  በቀጣይ በማስተካከል እና መልካም ልምዶችን በማስቀጠል የምርትና የገበያ ትስስሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ጀሞ አካባቢ የኤግዚቢሽን ማዕከል ለመገንባት የዲዛይን ሥራ የተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው፤ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አቅማቸው እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንሰራለን ነው ያሉት።

የባዛርና ኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች በተፈጠረላቸው የገበያ እድልና እርስበርስ የመተዋወቂያ መድረክ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በአገር አቀፉ የሞዴል ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ባዛርና ኤግዚቢሽን ከስድስት ክልሎች የተሳተፉ 186 ኢንተርፕራይዞች እና ስምንት ተቋማት እውቅና እና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም