የትንሣኤ በዓልን ስናከበር ለአገር ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት በመፀለይና መልካምነትን በተግባር በማሳየት ሊሆን ይገባል

143

ሚያዚያ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የትንሣኤ በዓልን ስናከበር ለአገር ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት በመፀለይና መልካምነትን በተግባር በማሳየት ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ተናገሩ።

የስቅለት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት እለት ማስታወሻ ሲሆን በዓሉ በዛሬው ዕለት በመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከብሯል።

በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ስለስቅለቱ የሚያወሱ ምንባባት ሲነበቡ፣ በስግደት፣ በጾምና በጸሎት ተከብሯል።

የስቅለት በዓልን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በስግደት፣ በፆምና በጸሎት እንዲሁም ክርስቶስ ለሰው ልጆች የከፈለውን ስቃይ በማሰብ ማክበር ችላለች።

የቤተክርስቲያኗ ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል የትንሣኤ በዓል የፍቅርና የይቅርታ ተምሳሌት በመሆኑ ሁላችንም ይህንኑ መልካም ተግባር በመፈፀም ልናከብረው ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን የፈተና ወቅት እንድታልፍ አማኞች ለአገር ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት አጥብቀው በመፀለይና መልካምነትን በማሳየት መሆን አለበት ነው ያሉት።

የጥላቻና ቂም በቀል አካሄድን በመተው ለአብሮነት፣ የአገርና የህዝብ ሰላም እውን መሆንን አስበን እንስራ ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የቤተክርስቲያኗ ካህን አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ፤ በዓሉ ሲከበር አንዱ ለሌላኛው ምህረት በማድረግና በጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን ይገባል ብለዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም