በፍቼና ነቀምቴ ከተሞች በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከ1ሺህ ለሚበልጡ ችግረኛ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ

111

ነቀምቴ/ፍቼ ፤ ሚያዝያ 14/2014(ኢዜአ) በፍቼና ነቀምቴ ከተሞች የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ከ1ሺህ ለሚበልጡ ችግረኛ ወገኖች የገንዘብ፣ ምግብና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ።

በፍቼ ከተማ   ለ556  ችግረኛ  ህፃናትና ቤተሰቦቻቸው የአካባቢው መንግስት ሰራተኞችና ሌሎች ነዋሪዎችን  በማስተባበር   ያሰባሰቡትን 275ሺህ ብር  በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን የድጋፍ አሳባሳቢው ጊዜያዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሃና ጠና ገልጸዋል።

የተደረገው ድጋፍ ለእያንዳንዱ  እስከ 1ሺህ ብር እና በተጨማሪም የአልባሳት ድጋፍ መደረጉም ተመልክቷል።

ለችግረኛ ወገኖች የተደረገው ድጋፍ ቀጣይነት ኖሮት በዘላቂነት ለማቋቋም ባለሀብቶችን በማስተባባር ጭምር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  የኮሚቴው አባል አቶ ማሞ በላቸው ናቸው።

ዕድሜያቸው 73 ዓመት እንደሆናቸውን የተናገሩት የፍቼ ከተማ ነዋሪ አቶ  ነገዎ ቢራቱ ፤በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የከተማው ህዝብ ያለውን በማካፈል በአልባሳትና በምግብ ላደረገላቸውም ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡  

በሌላ በኩል ጂጂ የዱቄት ፋብሪካ በነቀምቴ ከተማ ለሚገኙ ለ530  ችግረኞች ቤተሰቦች የበዓል መዋያ ዱቄትና የምግብ ዘይት ድጋፍ አድርጓል።

በዚህም  ለትንሳዔ በዓል መዋያ 5 ሺህ 300 ኪሎ ግራም የስንዴ ዱቄትና 530 ሊትር የምግብ ዘይት የፋብሪካው ባለቤቶች አቶ ግርማ ዓለሙና ባለቤታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ሐምቢሳ መስጠታቸውን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ገልጸዋል።

ተወካያቸው  አቶ ታሪኩ ብርሃኑ ፤ የፋብሪካው ባለቤቶች  ድጋፉን ያደረጉት  መስጠት ባህላችን ነው በማለት እንደሆነ ተናግረዋል።

ድጋፉም 524 ሺህ ብር እንደሚገመት ጠቁመው፤ ፋብሪካው የዛሬን ጨምሮ በየዓመቱ ለአቅመ ደካሞችና ሌሎች ችግረኛ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም አሰታውሰዋል።

የነቀምቴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባሕሩ ኤባ በበኩላቸው፤ ባለሀብቶቹ ካላቸው በማካፈል ለችግረኛ ወገኖች ለበዓል መዋያ ይህንን የመሰለ ድጋፍ ለስድስተኛ ጊዜ  በማድረጋቸው በአስተዳደሩ ስም እናመሰግናለን ብለዋል።

ሌሎች በከተማው የሚገኙ ባለሀብቶችም የጂጂ ዱቄት ፋብሪካን መልካም ተሞክሮ በመከተል የተቸገሩ ወገኖችን እንዲደግፉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ጀላኔ ቡሊ በድጋፉ መደሰታቸውን በመግለጽ የፋብሪካውን ባለቤቶች  አመስግነዋል፡፡

ወይዘሮ በልፌ በሪ በበኩላቸው፤ ለዓመት በዓል መዋያ በማግኘታቸው ደስተኛ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም