የኢዜአ ሰራተኞች የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሁለት የአገር ባለውለታ ቤተሰቦችን ጠየቁ

129

ሚያዚያ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሰራተኞች የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሁለት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ቤተሰቦችን ጠየቁ።

ላብ ከደም ገብሮ ሀገርን በክብር ለማቆም ከቆረጠ ሰው በላይ ጀግና ከወዴት ይገኛል?

ለሀገር ወጥቶ ከማደር፣ ለሉዓላዊነቷ እንቅልፍ ከማጣት፣ ለነጻነቷ ከመሰዋት በላይስ የሀገር ፍቅር በምን ይገለጻል?ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የመጨረሻ ምሽግ የሆነው የአገር መከላከያ ሰራዊት የጀግንነት መገለጫና የአገር ክብር ዋስትና መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ክብርና ማዕረግ የሕዝቦች ሰላም ተጠብቆ እንዲቀጥል ከጠላት ጋር በጀግንነት በመፋለም የታሪክ አሻራቸውን አኑረው ከተሰዉ የሰራዊት አባላት መካከል ኢዜአ የሁለት ጀግና ወታደሮችን ታሪክ ከወራት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።

ሻለቃ አብይ ጋሹ እና ሻለቃ እያሱ ሽመልስ፤ ጠላትን በጀግንነት በመፋለም ታላቅ ጀብድ ፈፅመው ያለፉ የምን ጊዜም ጀግኖች ናቸው።

እነዚህ የጦር መሪዎች በተሰለፉባቸው አውደ-ውጊያዎች ሁሉ ክንደ ብርቱነታቸውን ያስመሰከሩ በጀግንነት ሰገነት ላይ የወጡ ለሀገራቸው ክብር ሕይወታቸውን የሰጡ ባለውለታ ናቸው።

መንግሥት በሕልውና ዘመቻው ለተሰዉ የሠራዊት አባላት እውቅና በሰጠ ጊዜ ሻለቃ አብይ ጋሹ እና ሻለቃ እያሱ ሽመልስ በጦር ሜዳ የላቀ ጀብድ ተሸላሚ በመሆን የአንደኛ ደረጃ የላቀ ጀግና ሜዳሊያ ሽልማት ቤተሰቦቻቸው መረከባቸው ይታወሳል።

እነዚህ ጀግኖች ስለ አገር ፍቅር የተዋደቁ፣ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ክብር ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ እና የአገር ፍቅርን የላቀ ስሜት አጋርተው ያለፉ ጀግኖች ስለመሆናቸው በልጆቻቸው አንደበት ተመስክሮላቸዋል።

በመሆኑም የእነዚህን ጀግና የሀገር ባለውለታ ቤተሰቦች ኢዜአ የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ስጦታ አበርክቶላቸዋል።

የጀግና ቤተሰብ በመሆናችን ሁሌም ኩራት ይሰማናል፤ በአካል አብረውን ባይኖሩም የፈጸሙት ጀግንነትና ያወረሱን ፅናት ለዘላለም አብሮን ይዘልቃል ሲሉ ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።

ኢዜአ የትንሣኤ በዓልን በማስመልከት ስለጠየቃቸውም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ የአገር ባለውለታ የሆኑ የጀግና ቤተሰቦችን መጠየቅ እና መደገፍ አስፈላጊ እና የግድ መሆኑን ተናግረዋል።

ሻለቃ አብይ እና ሻለቃ እያሱ ታሪክ የማይዘነጋው ጀግንነት ፈፅመው ያለፉ የቁርጥ ቀን ልጆች በመሆናቸው ቤተሰቦቻቸውን የመጠየቅና የመደገፍ ኃላፊነት የሁላችንም ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

እነዚህ ጀግኖች ታሪክ ሰርተው ታሪክ ያኖሩ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያን ያዳኑ ታላቅ የአገር ባለውለታ በመሆናቸው ኢዜአ ቤተሰቦቻቸውን በቀጣይ ለመደገፍ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በቋሚነት ለሚደግፋቸው 18 ህፃናት በትላንትናው እለት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም