በሶዶ ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ላሉ ህፃናት የማዕድ ማጋራትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

105

ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዚያ 14/2014 (ኢዜአ)…የደቡብ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮና ሆፕ ፎር ጀስቲስ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በወላይታ ሶዶ ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ህፃናት የማዕድ ማጋራትና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ አደረጉ።

የደቡብ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮና ሆፕ ፎር ጀስቲስ ያደረጉት የማዕድ ማጋራትና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳላቸው ተገልጿል።

የደቡብ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ በተለያየ ምክንያት ከወላጆቻቸው ተለይተው በወላይታ ሶዶ ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ 40 ሕፃናት ከ300 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ በይዳ ሙንዲኖ እንደገለጹት ቢሮው ሕፃናቱ ከወላጆቻቸው እስኪቀላቀሉ ድረስ መልካም ቆይታ ማድረግ እንዲችሉ  ድጋፉን ያደረገው ኅብረተሰቡንና አጋር አካላትና በማስተባበር ነው።

ኃላፊዋ እንዳሉት በተለያየ ምክንያት ወደ ጎዳና የወጡ ህፃናትን በመደገፍ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመቀላቀል እየተሰራ ቢሆንም ወደ ጎዳና የሚወጡ ህፃናት ቁጥር በሚፈለገው ደረጃ እየቀነሰ አይደለም።

በመሆኑም ለጎዳና የሚዳርጋቸውን ስጋት ከምንጩ ለመቀነስ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

በተመሳሳይ ሆፕ ፎር ጀስቲስ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከደቡብ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ከ280 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ማዕድ ማጋራቱን የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰላሙ ይገዙ ገልጸዋል።

ድርጅቱ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጎዳና የወጡ ህጻናትን አንስቶ እንዲያገግሙ በማድረግ ከመንግሥት አካላት ጋር በመሆን ወደ ቤተሰቦቻቸው የመመለስ ስራ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህም ባሻገር ድርጅቱ ለወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚያወጣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ አድርጓል።

ድርጅቱ ድጋፉን ያደረገው በዞኑ ለሚገኙ 60 ትምህርት ቤቶች መሆኑን የድርጅቱ ሥራ አስኪጅ አቶ ሰላሙ ይገዙ ገልጸዋል።

የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ኩማ በበኩላቸው በተለያየ ምክንያት ወደ ጎዳና ከሚወጡ ህፃናት አብዛኞቹ በትምህርት ገበታ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፤ በድርጅቱ የተደረገው ድጋፍ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ለመማር ማስተማር ስራ አጋዥ ነው ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በአካባቢው ህፃናት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይለዩ እያደረገ ላለው ድጋፍ በዞኑ ትምሀርት ማህበረሰብ ስም አመስግነው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም