"ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት ጥሪ"ን ተከትሎ ከተለያዩ የአለም አገራት እንግዶች እየገቡ ነው

83

ሚያዝያ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት ጥሪ"ን ተከትሎ ከተለያዩ የዓለም አገራት እንግዶች ወደ አገር ቤት እየገቡ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ቀደም ሲል ኢድን በአገር ቤት እናክብር በማለት "ታላቁ የኢድ ሰላት በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል ለኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ወዳጆች ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ከተለያዩ የዓለም አገራት ኢድን በአገር ቤት ለማክበር እንግዶች አዲስ አበባ በመግባት ላይ ይገኛሉ።

በቀረበው ጥሪ መሰረት ኢድን በጋራ እያከበርን፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመጠየቅና በማገዝ ጥሩ ቆይታ ልናደርግ መጥተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው እንግዶች ገልጸዋል።

በተለይ በጦርነት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ተዘዋውሮ በመጎብኘት አቅማቸው የቻለውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በመንግስት የተደረገው ጥሪ ወገኖችን ከማገዝ በተጨማሪ ቤተሰብን አግኝቶ ኢድን በጋራ ለማሳለፍም ልዩ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢድን በጋራ ለማክበር የተገኙት ወገኖቻችን በቆይታቸው የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ወደ መጡበት ሲመለሱ ደግሞ የአገራቸው አምባሳደር በመሆን የኢትዮጵያን እውነታ የሚያስረዱ መሆኑን  ከኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢ ዑስታዝ አቡበክር አህመድ ገልጸዋል።

ለኢድ የሚመጡት በዓሉን አክብረው በአገራቸውም ኢንቨስት የማድረግ እድል እንዲያገኙ እየተመቻቸላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ከኢድ እስከ ኢድ የጎረቤት አገራት የእምነቱ ተከታዩች እና የሃይማኖት መሪዎች ጥሪ የተደረገላቸው መሆኑንም ኡስታዝ አቡበከር አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ትልቅ ድርሻ ያላትና ታሪካዊ አገር በመሆኗ ዓለም በቅጡ እንዲያውቃት የሁላችንም ጥረት ሊታከልበት ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የዘንድሮው 1 ሺህ 443ኛው የኢድ-አልፈጥር በዓል በመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከሳምንት በኋላ የሚከበር ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም