ርዕሰ መስተዳደሩ ህዝቡ በዓሉን ሲያከብር በፍቅርና አብሮነት የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ እንዲሆን መልዕክት አስተላለፉ

146

ሀዋሳ ፤ ሚየዚያ 14/2014 (ኢዜ) የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር በፍቅርና አብሮነት አቅመ ደካማና ጧሪ የሌላቸውን ወገኖችን በመደገፍ እንዲሆን መልዕክት አስተላለፉ።

ለክርስትና እምነት ተከታዮች ለስቅለትና ትንሳኤ በዓል የእንኳን  አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ፤ ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ የሰላም ምንጭና መሰረት በመሆኑ በዓሉን ስናከብር ከጥላቻ በመራቅ እርስ በእርስ መተሳሰብ የሚጎላበት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።

"ለጠላቶቻችን እኩይ ሴራ ሳንበረከክና ሳንበገር የሀገራችንን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ከምንም ጊዜ በላይ አንድነታችንን አጠናክረን ማስቀጠል የሚገባን ጊዜ ላይ ነን" ሲሉም ገልጸዋል።

ክርስቶስ ባስተማረን ፍቅር ራስን በማነጽ ከዘረኝነት፤ ጥላቻና ፅንፈኝነት በመላቀቅ እርስ በእርስ በመግባባት ላይ የተመሰረተ የውስጥ አብሮነትንና አንድነትን ማጎልበት ይገባናል ነው ያለት ርዕሰ መስተዳድሩ።

ከግላዊ ጥቅምና ፍላጎት በመላቀቅ፣ በመተጋገዝና በመተሳሰብ በታማኝነትና በቅንነት ህዝብን በማገልገል ለሀገር ያለንን ፍቅር በተግባር መግለጽም እንዲሁ።

"ሁሉም ጠንክሮ በመስራትና ለሀገር እድገት የሚጠቅም ልማትን በማስቀጠል ጠንካራ የሆነች ሕብረ ብሔራዊት  ኢትዮጵያን ገንብቶ ወደ ብልፅግና ማማ ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ለአቅመ ደከማ ወገኖች ማዕድ በማጋራትና ጧሪ የሌላቸውን አረጋዊያን በመደገፍ እንዲሆነም  መልዕክት አስተላልፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም