ህዝቡ በዓሉን ሲያከብር በአንድነትና ፍቅር ተሳስቦ ሊሆን ይገባል- የኃይማኖት አባቶች

142

ሀዋሳ ፤ ሚያዚያ 14/2014 (ኢዜአ)ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳዔን በዓል ሲያከብር ከክርስቶስ የተጎናጸፈውን ፀጋ ጠብቆ በአንድነትና ፍቅር ተሳስቦ ሊሆን እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

በበዓሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች በተለያዩ ምክንያት የተፈናቀሉና የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ መደገፍ እንደሚኖርባቸውም ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሲዳማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ ህዝቡ በዓሉን ሲያከብር ከክርስቶስ የተጎናጸፈውን ፀጋ በመንተራስ በአንድነት እና በፍጹም ወንድማዊ ፍቅር መሆን አለበት።

ከክርስቶስ ጸጋዎች መካከል  የሰው ልጆች  ከጨለማ ወደ  ብርሀን የወጡበት ፣ከሞት  ወደ ህይወት የተሸጋገረበት፣ እንዲሁም ሙታን የነበርን በክርስቶስ ሞትና ትንሳዔ ህያዋን ሆነናል ብለዋል።

የዛሬው ዕለተ አርብ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ባለው ታላቅ ፍቅር መሰቀሉን የምንዘክርበት ነው ያሉት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ምዕመኑም እንደ አምላክ ፍቅርን በመላበስ ከሁሉም የሰው ልጆች ጋር በሰላም መኖር እንዳለበት አመልክተዋል።

ህዝበ ክርስቲያኑ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር  በሰላምና  በፍቅር  በመኖር  ሃይማኖታዊ ግዴታውን ከመወጣት ባሻገር የትንሳዔ በዓልን ሲያከብር የመረዳዳት ባህሉን በማጠናከርና ከጥላቻ በመራቅ በመተሳሰብና በአብሮነት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ትንሳኤ ለሰው ልጆች ሁሉ ከመከራ የመነሳት የተስፋ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ ስለሆነ እኛም አሁን የገጠሙንን የውስጥና የውጭ ችግሮች ተቋቁመን ፈተናዎችን በፅናት ለመሻገር መነሳት ይኖርብናል ብለዋል።

የሀዋሳ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና መጋቢና የወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት መሪ ፓስተር ጌቱ አያሌው በበኩላቸው፤" የትንሳዔ በዓል ለኛ ክርስቲያኖች ያለው ዋጋ ታላቅ ነው" ብለዋል።

“ጌታችንና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ሲል መከራና ስቃይን ተቀብሎ ፍቅርን እንዳስተማረን እኛም እርስ በእርስ ልንዋደድ ይገባል” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የትንሳዔ በዓልን ስናከብር  የፍቅር፣የሰላምና የእርቅ መንፈስን ተግባራዊ በማድረግ እና ጥላቻን ማስወገድ ይኖርበናል ነው ያሉት።

የእምነቱ ተከታዮች  በተለያዩ ምክንያት የተፈናቀሉና የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ፣ በገንዘብ ፤ በአልባሳትና በምግብ መደገፍ እንደሚኖርባቸውም አመለክተዋል።

በከርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የትንሳዔ በዓል በመጪው እሁድ እንደሚከበር ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም