የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞዋ እንዲሳካ ሴቶች በተደራጀ አግባብ ሚናችን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

165

ደሴ /ኢዜአ/ ሚያዚያ 13/2014 ''ኢትዮጵያ ከገጠማት ውስብስብ ችግር ታላቃ የብልፅግና ጉዞዋ እውን እንዲሆን ሴቶች በተደራጀ አግባብ ሚናችን ልንወጣ ይገባል'' ሲሉ የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ህሌና መብራቱ አስገነዘቡ፡፡

የደሴና የደቡብ ወሎ ዞን ሴቶች "እኛ ሴቶች የጉባኤ ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ እንተጋለን፣ እናተጋለን" በሚል መሪ ቃል በደሴ ከተማ ዛሬ ምክክር አካሂደዋል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ህሊና መብራቱ በመድረኩ እንዳሉት በህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛ ነው፡፡

ኢትዮጵያን እየተፈታተኑ ያሉ ውስብስብ ችግሮች ተፈተው የተጀመረው የብልፅግና ጉዞ እውን እንዲሆን  ሴቶች የማስማማትና የብልሃት ጥበባቸውን በመጠቀም ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ስራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የሰላም እጦት፣ ፅንፈኝነት፣ የሴራ ፖለቲካና ሌሎች ችግሮችም እየተበራከቱ መምጣታቸው በተለይ በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጫና ከባድ በመሆኑ በጋራ እንታገላለን ሲሉ በአፅኖት ተናግረዋል፡፡

ባል፣ ልጆቻችን፣ ወንድሞቻችንና ቤተሰቦቻን ሁሉ በአፍራሽ ተግባር እንዳይሳተፉ ከማድረግ ባለፈ አንድነትና አብሮነትን እንዲያስቀጥሉም በየቤታችን መምከርና መገሰፅ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በከተማ ግብርናም በየግቢያችን ባሉ ክፍት ቦታዎችና በየግድግዳው ሁሉ በወዳደቁ ፕላስቲኮች የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የኑሮ ወድነቱን ለማረጋጋትም ሚናችንን ልንወጣ ግድ ነው ይላሉ፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የደሴ ከተማ አስተዳደር የሴቶች ሊግ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አብዮት ጋሻው በበኩላቸው በሴቶች ላይ የሚደርሱ በደሎች ለማስቀረት ከምናደርገው ትግል ባለፈ የኢትዮጵያ ችግር እንዲፈታ ተባብረን የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

የስራ አጥ ሴቶችን ቁጥር ለመቀነስ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸው ለማሳደግና ሁለተናዊ ተጠቃሚነታቸውን በተግባር ለማረጋገጥም ከመንግሥት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሀገር ዘራፊ ሌቦችን፣ ጥቅመኛ አመራሮችን፣ በመካከላችን ያሉ ሀገር አፍራሽ ሴረኞች አጋልጠን በመስጠት የብልፅና ጉዟችንን እውን ለማድረግ ሴቶች ቁርጠኛነታችን በተግባር ማሳየት ይገባል ብለዋል።

በፓርቲ ጉባኤው የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተረድቷል፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና በደሎችንም ተገንዝቧል፤ በየደረጃ ፈጣን ምላሽ ግን ሊሰጥ ይገባል ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ዘይባ የሱፍ ናቸው፡፡

ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት የሚደረገውን ጥረትም በመደገፍ ለውጡን ወደ ታች ለማውረድ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

በተለይ አንድነትና ሰላምን በማጠናከር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት እናደንቃለን፣ እንደግፋለንም ሲሉም ገልፀዋል።

ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ መሰረት ታደሰ በበኩላቸው ፓርቲው በየጊዜው የሴቶችን ተጠቃሚነት አረጋግጣለሁ ከሚል ተስፋ መስጠት በፍጥነት ወጥቶ ወደ ተግባር መግባት አለበት ብለዋል፡፡

በተለይ እያሻቀበ የመጣው የኑሮ ውነት፣ የሰላም እጦት፣ የሴራ ፖለቲካ ችግሮች በዋናነት ሴቶችን እየጎዱ በመሆናቸው እልባት እንዲበጅላቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም