60 ሽህ 200 ሃሰተኛ የብር ኖት ይዞ ግብይት ለመፈፀም የሞከረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ - ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
60 ሽህ 200 ሃሰተኛ የብር ኖት ይዞ ግብይት ለመፈፀም የሞከረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ - ፖሊስ
ባህር ዳር ሚያዚያ 13/2014- (ኢዜአ ) በባህር ዳር ከተማ 60 ሽህ 200 ሃሰተኛ የባለ 200 ብር ኖት በመያዝ ግብይት ሊፈጽም የሞከረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
በባህር ዳር ከተማ የ4ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ጽፈት ቤት ሃላፊ ኮማንደር ጥሩነህ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት ተጠርጣሪ ግለሰቡ ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ከሃሰተኛ የብር ኖቱ ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል።
ግለሰቡ በከተማው ቀበሌ 17 በሚገኘው የገበያ ቦታ በግ ለመግዛት ሲንቀሳቀስ ዛሬ እኩለ ቀን በፀጥታ ሃይሎች መያዙን ገልፀዋል።
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት 60 ሽህ 200 ሃሰተኛ የባለ 200 ብር ኖት ይዞ መገኘቱን ተናግረዋል።
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በህግ እየተጣራ መሆኑን የጠቀሱት ኮማንደሩ ህብረተሰቡ በበዓል ወቅት ሊደርስ ከሚችል መሰል ማጭበርበር ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ የማጭበርበርና ዝርፊያ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ ተገቢው የፀጥታ ጥበቃ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በመቀናጀት የትንሳኤ በዓል በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር የጀመረውን የጸጥታ ማስከበር ስራ እአጠናከሮ እንዲቀጥል ሀላፊው ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል የትንሳኤ በዓል በሰለማዊ መንገድ እንዲከበር ተገቢው የፀጥታ ማስከበር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርን በመጥቀስ ኢዜአ በዛሬው እለት መዘገቡ ይታወቃል።