ጤና ቢሮው በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

51

ሰቆጣ ኢዜአ ሚያዚያ 13/2014 ዓ/ም የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድሐኒትና ህክምና ቁሳቁስን ድጋፍ ዛሬ አደረገ።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ተወካይ አቶ ዓለሙ ታፈሰ በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ድጋፉ የተደረገው በዞኑ አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት የደረሰውን ጉዳት ለማገዝ ነው።

በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት አቅም በማጠናከር ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻልም የመድሃኒት፣ የህክምና እና የቢሮ ቁሳቁስን ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።

ድጋፉ አልትራ ሳውንድ፣ ዘመናዊ ህሙማን መተኛ አልጋ፣ የውስጥ ደዌ መመርመሪያ መሳሪያ፣ የቀዶ ሕክምና፣ የሰመመን መስጫና የመተንፈሻ መሳሪያዎች ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።
ቢሮው የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት ወደ ቀደመ አገልግሎታቸው እስኪመለሱ ድረስም ድጋፉን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ሃላፊ ዶክተር ኪዳት አየለ በበኩላቸው አሸባሪው ህውሓት ወረራ በፈፀመበት ወቅት በርካታ የጤና ተቋማትን ዘርፏል፤ አውድሟል ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ በዞኑ በሚገኙ ከጤና ኬላ እስከ ሆስፒታሎች ደረጃ ባሉ ጤና ተቋማት ወደ 390 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያላቸው የህክምና መሳሪያዎችን ማውደሙንና መዝረፋን ገልፀዋል።

የጤና ተቋማቱን መልሶ በማቋቋም ለህብረተሰቡ የተሻለ የህክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ያደረገው ድጋፍም ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ወደ ቀደመ አገልግሎት ከመመለስ ባሻገር የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ለማሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የችግሩን ስፋት በመረዳት ላደረገው ወገናዊ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በዞኑ በሽብር ቡድኑ የተዱ የጤና ተቋማትን ወደ ስራ ለማስገባት እየተደረገ ያለውን ጥረት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም