በክብር ለተሰናበቱ ለ528 የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በአርባ ምንጭ ከተማ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተሰጠ

220

አርባ ምንጭ ፤ ሚያዚያ 13/2014 (ኢዜአ) የአገልግሎት ጊዜያቸውን በማጠናቀቅ በክብር ለተሰናበቱ ለ528 የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተሰጠ።

ለሰራዊቱ  አባላት የጋራ መኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታውን የሰጠው የከተማዋ አስተዳደር ነው።

የአስተዳደሩ  ከንቲባ አቶ ማርቆስ ማቴዎስ በወቅቱ እንዳሉት፤ የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በ90 ቀናት ካስቀመጧቸው ዕቅዶች መካከል የመከላከያ ሰራዊት የመኖሪያ ቤት ችግር መፍታት  አንዱ ነው፡፡

በዚህም   በ37 ማህበራት የተደራጁ ለ528 ተሰናባች የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ለቤት መስሪያ የሚሆን 52 ሺህ 800 ካሬ ሜትር መሬት መሰጠቱን አረጋግጠዋል፡፡

በሀገር መከላከያ ሰራዊት በመቀላቀል የሚችሉትን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈሉ የሰራዊቱ አባላት በሚደረገው ድጋፍ አስተዳደሩ ደስ እያለው የሚያደርገው መሆኑን ካንቲባው አስታውቀዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከተደራጁ በኋላ 5 በመቶ ቁጠባ ማስቀመጥ እንዲችሉ 84 ሺህ ብር የጋሞ ዞን አስተዳደር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በ90 ቀናት ዕቅዳችን መሠረት ከመጪዉ ሣምንት ጀምሮ መስፈርቱን ለሚያሟሉ መምህራንና ሌሎች ማህበራት የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ስፍራ እንደሚሰጡ ከንቲባው ይፋ አድርገዋል፡፡

የቤት መስሪ ቦታ ከተሰጣቸው የሰራዊቱ አባላት መካከል ዓለማየሁ ኢያሱ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ከ1992 እስከ 1997 ዓ.ም  ወደ ሰራዊቱ በመቀላቀል ሀገራቸውን በማገልገላቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

የሰራዊት አባል ሆኖ ለሀገር መስዋዕትነት መክፈል መታደል ነው ያሉት፤ አስተያየት ሰጪው፤ የአገልግሎት ጊዜውን  በማጠናቀቅ በክብር መሰናበታቸውን አመልክተዋል፡፡

ተረስተው የነበሩበት ሁኔታ ከለውጡ በኋላ በመንግስት ትኩረት በማግኘት  ለሀገራቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ  የጋራ መኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ዛሬ መረከብ በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ ምላሽ በማጣት የመልካም አስተዳደር ችግር እንደነበር የተናገሩት ደግሞ ሌላው የሰራዊቱ አባል አስር አለቃ አበበ ቦርቻ ናቸው፡፡

ከብዙ ዓመታት በኋላ  ዛሬ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ማግኘት በመቻላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም