የሻሸመኔ ነዋሪዎች አሸባሪውን ሸኔ በፅናት ታግለው እኩይ ዓላማውን እንደሚያመክኑ አስታወቁ

113

ሻሸመኔ፣ ሚያዝያ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው አሸባሪውን ሸኔን በፅናት በመታገል እኩይ ዓላማውን እንደሚያመክኑ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።

አሸባሪው ሸኔ ንጹሃንን በመግደል፣ ሀብት ንብረት በመዝረፍና በማውደም እኩይ ተግባር እየፈጸመ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ሸኔ በተባለው ቡድን የሚፈጸም ግድያ እና ማፈናቀል እንዳንገሸገሻቸው ገልጸዋል።

ቡድኑ የሕዝብ ስጋት እንዳይሆን ለማድረግ በሚካሄደው ሁሉን አቀፍ ትግል ከመንግስት ጎን ሆነው የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል።

መንግሥት በሽብር ቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ትክክል እንደሆነ ገልጸው፤ የጥፋት ቡድኑን መግቢያ መውጫ ተከታትለው ለፀጥታ አካላት ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

አሸባሪው ሸኔን ለማጥፋት እየተደረገ ላለው ጥረት የህዝብ ንቁ ተሳትፎ  ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በምዕራብ አርሲ ዞን ሄባን አርሲ ወረዳ ሲንቀሳቀስ የነበረውን የአሸባሪው ሸኔ ቡድን የአካባቢው ህዝብ ከመንግሥት የፀጥታ አካላት ጎን ተሰልፎ ማስወገድ መቻሉን በአብነት አንስተዋል።

ሄባን አርሲ ወረዳን ሕዝብ ተሞክሮ በማስፋት በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚሽሎከለከውን የሽብር ቡድን ማስወገድ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞን ባህል፣ ወግና ሥርዓት የማያከብርና የማይወክል የሽብርተኞች ስብስብ ቡድን በመሆኑ በጋራ ትግል እንዲጠፋ ለማድረግ ትግላቸውን አጠናከር እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም