በክልሉ የስቅለትና የትንሳኤ በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት እየተደረገ ነው - የፖሊስ ኮሚሽን

98

ሀዋሳ ፤ሚያዚያ 12/2014 (ኢዜአ) በክልሉ መጪው የስቅለትና የትንሳኤ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ እንደገለጹት፤ ሚያዚያ 14 እና 16/ 2014 ዓ.ም የሚከበረው የስቅለትና የትንሳዔ በዓል በሰላም እንዲከበር ከኃይማኖት አባቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጀት እየተሰራ ነው።

ቀጥሎ የሚከበረውን የኢድ አልፈጥር በዓልም በሰላም እንዲከበርም እንዲሁ።

በክልሉ የሚገኙ የጸጥታ አካላት የጋራ እቅድ አውጥተው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ህዝቡን ከጎኑ አሰልፎ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በየደረጃው የፀጥታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይ ህብረተሰቡ ለበዓል ወደ ቤተሰብ በሚጓዝበት ወቅት በትራንስፖርት ላይ ያልተገባ የታሪፍ ጭማሪ፣የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖር፣ በበዓል ግብይት ላይ የማጭበርበር ወንጀሎችን ለመከላከል ፖሊስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ሰላምን ለማስጠበቅና ወንጀልን ለመከላከል የጸጥታና የህግ አስከባሪ አካላት በቅንጅት እንደሚሰሩ ህብረተሰቡ አውቆ ለእነዚህ አካላት አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዳለበት ኮሚሽነር አለማየሁ አሳስበዋል።

በክልሉ በደቡብ ኦሞና አማሮ አካባቢዎች ሰሞኑን የተከሰቱ የፀጥታ ችግር መኖሩን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ መንግስት በአካባቢዎቹ ከመደበኛው ፖሊስና ልዩ ኃይል በተጨማሪ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ህብረተሰቡ ደህንነት እንዲሰማው የማረጋጋት ተግባርን በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

በፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች በዓልን በደስታና በአንድነት እንዲያከብሩ መንግስት እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

መላው ህብረተሰብም ለተፈናቀሉ ወገኖች በማካፈል በዓሉን በአብሮነት እንዲያከብሩ ኮሚሽነር አለማየሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም