በምዕራብ ጉጂ ዞን ከ30 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች እየተተከሉ ነው

199

ዲላ፣ ሚያዚያ 12/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ጉጂ ዞን ከ30 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ተከላ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ኡደሳ ቦጋለ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ በመተከል ላይ ያሉት የቡና ችግኞች ዝርያቸው ከተለመደው የቡና ዝርያ ባጠረ ጊዜ ምርት እንደሚሰጡ በምርምር የተረጋገጠ ነው። 

በዞኑ ስድስት ወረዳዎች በ100 ሺህ ሄክታር ላይ የሚተከሉት የቡና ችግኞች በሽታን ተቋቁመው ጥሩ ምርት በመስጠት የቡና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።

ከተለያዩ የግብርና የምርምር ተቋማት የተገኙት አዳዲሶቹ የቡና ዝርያዎች በሄክታር ከ12 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰጡም ገልጸዋል።

በዚህም በተለምዶ በሄክታር ከአምስት ኩንታል ያልበለጠውን ምርት ከእጥፍ በላይ እንደሚያሳድጉት ኃላፊው አስረድተዋል።

በዞኑ በሚገኙ ከ50 በላይ ችግኝ ጣቢያዎችና በአርሶ አደሮች ማሳ ተዘጋጅተው እየተተከሉ ያሉት የቡና ችግኞች ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት ባለው ጊዜ ለምርት እንደሚደርሱ በምርምር መረጋገጡን ተናግረዋል።

ከችግኞቹ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በሐምሌ ወር ይተከላሉ ብለዋል።  

ተከላውን ለማከናወን ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የነበረና ምርት የማይሰጥ ያረጀ ቡና ነቀላ መከናወኑን አቶ ኡደሳ አስረድተዋል።

በተጓዳኝ የቡና እርሻ ማስፋት፣ የጉድጓዶች ቁፋሮና አርሶ አደሮች ያዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ  ማቀላቀል ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም