በክልሉ በ35 ሚሊዮን ብር ተግባራዊ የሚደረግ የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ተጀመረ

231

ሐረር ሚያዝያ 12/2014 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል በ35 ሚሊዮን ብር ተግባራዊ የሚደረግ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ዛሬ በይፋ ተጀመረ።

መርሃ ግብሩ ህጻናት ትምህርታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ መሰረታዊ  ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችላቸው ተገልጿል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ እንደተናገሩት በመርሃ-ግብሩ  ከቅድመ መደበኛ እስከ አራተኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።

በመርሃ-ግብሩ በገጠርና በከተማ  በ67 ትምህርት ቤቶች  35 ሺህ  ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል ፡፡

የክልሉ መንግሥት ለመርሃ ግብሩ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም  600  የተማሪ ወላጆች በመርሃ- ግብሩ ሥራ እንደተፈጠረላቸው ሃላፊው አመልክተዋል ፡፡

"መርሀ ግብሩ የተማሪ ወላጆች የኢኮኖሚ አቅም አንዲያድግና እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ያደርጋል" ሲሉም አክለዋል፡፡

መርሃ-ግብሩ  ቀጣይነት  እንዲኖረው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ባለሀብቶችን በማስተባበር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አቶ ሙክታር አስታውቀዋል።

"ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥ ምግብ ማግኘታቸው በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ፣ የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስና ጤናማ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር ያግዛል" ብለዋል ፡፡

የራስ መኮንን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ ሼዙ መሐመድ በበኩላቸው መርሃ ግብሩ  በችግር ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።

በመማር ማስተማር ሂደት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያበቃቸውም ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ሥራ ከተፈጠረላቸው የተማሪ ወላጆች መካከል ወይዘሮ እፁብገነት ማሞ በመርሃ ግብሩ ''ልጆቼን እንድመግብና እኔም የሥራ እድል እንዳገኝ ሆኛለሁ'' ብለዋል።

መርሃ ግብሩ የታመለትን ግብ እንዲመታ ከሚመለከታቸው ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በመርሃ-ግብር ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም