ለትንሳዔ በዓል ጤንነቱና ጥራቱን የጠበቀ የእርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል

80

ሚያዚያ 12/2014 (ኢዜአ) ለትንሳዔ በዓል ጤንነቱና ጥራቱን የተጠበቀ የእርድ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ገለጸ።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፣ የሉኳንዳዎችና የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ማኅበር ለትንሳዔ በዓል እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰይድ እንድሪስ እንደገለጹት፤ ለትንሳዔ በዓል ጤንነቱ የተረጋገጠ የእንስሳት እርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል።

ማንኛውም አካል የተመረመረና ጤንነቱ የተረጋገጠ የቁም እንስሳት ማቅረብ ከቻለ ድርጅቱ የእርድ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

ድርጅቱ የበሬ ሥጋ በችርቻሮ እንዲሁም የበግና የፍየል ሥጋ ደግሞ በጅምላ እንደሚያቀርብ ጠቁመው ለዚህም 3 ሺህ የዳልጋ ከብት እንዲሁም 5 ሺህ የሚጠጉ ፍየልና በጎች ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ጎን ለጎንም ከአጎራባች ቄራዎች ጋር በትብብር ለመሥራት ሥምምነት መደረጉን ጠቅሰዋል።  

ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች መኖራቸው ገልጸው ኅብረተሰቡ ከቄራ ውጭ የሚፈጸም የእርድ ሥጋን ባለመጠቀም ራሱን ከበሽታ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

በከተማዋ በሚገኙ አራት የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከላት ከ30 እስከ 40 ሺህ የእርድ እንስሳትን ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ማኅበር ፕሬዘዳንት ወይዘሮ መዓዛ ቀለመወርቅ ናቸው።

የእርድ እንስሳቱን ለማቅረብ በተለይ ከአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ጋር ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ሉኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ፕሬዘዳንት አቶ አየለ ሳህሉ በበኩላቸው እርዱን በቄራዎች ድርጅት ለማከናወን የሚያስችል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም