ኢትዮጵያ የስንዴ ፍላጎቷን በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን የምታደርገው ጥረት ትክክለኛ አቅጣጫ የተከተለ ነው

412

ሚያዝያ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)  ኢትዮጵያ የስንዴ ፍላጎቷን በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን የምታደርገው ጥረት ትክክለኛ አቅጣጫ የተከተለና ለውጤት የሚያበቃ መሆኑን ዓለም አቀፍ የበቆሎና የስንዴ ማሻሻያ ማዕከል ገለጸ።

የማዕከሉ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር በቀለ አበዮ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት በርካታ ሥራዎች እያከናወነች ነው።

ለዚህም ደግሞ የኩታ ገጠም የግብርና ሥራና የመስኖ ልማት ሥራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመው ይህም አገሪቱ በትክክለኛ የግብርና አቅጣጫ ላይ መሆኗን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለስንዴ ምርት የሚሆን ከፍተኛ የውኃና የመሬት አቅርቦት እንዳላት ተናግረው መንግሥት ይህንን ኃብት በሙሉ አቅሙ መጠቀም ከቻለ ውጤታማ ሥራ መሥራት ይችላል ነው ያሉት።

ያም ብቻ ሳይሆን አገሪቱ በስንዴ እርሻ ሥራ ላይ እያሳየች ያለውን ጥረት ማስፋት ከቻለች በአጭር ጊዜ ውስጥ 'በምግብ ራስን መቻል' የሚለውን ትልቅ እቅድ ማሳካት እንደሚቻል ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ለውጭ ንግድ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችም ሊኖሩ እንደሚችሉ በመጠቆም።  

እንዲያም ሆኖ መንግሥት አሁንም ለዘርፉ እድገት ትኩረት በመስጠት በተለይም ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ማዳበሪያ የሚቀርብበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ትክክለኛውን ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም ድጋፍ ማድረግ፤ ተመራማሪዎች ከአከባቢው ሥነ-ምህዳር ጋር ተስማሚ የሆኑ መፍትሄዎችን ሊያበጁ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አርሶ አደሮችም ከመንግሥትና ከግብርና ባለሙያዎች የሚቀርቡላቸውን ምክረ ሃሳቦች በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ምርታቸውን ማስፋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሴቶች ከሕዝብ ቁጥር አንጻር ሰፊ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ የሴቶች የግብርና ተሳትፎም መጠናከር እንደለበት ጠቅሰዋል።  

ማዕከሉም በኢትዮጵያ ሥራ ከጀመረበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1987 ጀምሮ እስካሁን የተሻሻሉ የበቆሎና የስንዴ ምርቶች ለአርሶ አደሮች እያቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይ በተለይም በስንዴ ምርት ላይ ያለውን የድጋፍ ተደራሽነት በማስፋት የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።      

መንግሥት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን በአፋር፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በሚገኙ ዝቅተኛ ሥፍራዎች ላይ የበጋ ስንዴ ልማት ሥራ እያከናወነ ነው።   

መንግሥት ዘንድሮ በ400 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የበጋ ስንዴ ልማት እያካሄደ ሲሆን 16 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ በየዓመቱ 17 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ከውጭ ታስገባለች።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም