ዩኒየኑ ለአርሶ አደሩ የግብርና ግብዓቶችን በብድር በማቅረብ የጀርባ አጥንት ሆኗል

102

ሚያዝያ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሎሜ አዳማ የገበሬዎች ኅብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን ለመኸር እርሻ ግብዓት በብድር እያቀረበላቸው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ገለጹ።

ዩኒየኑ በሞጆ አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓቶች እና ዘመናዊ የእርሻ መሳርያዎች ትራክተርና ኮምባይነር እያቀረበ መሆኑንም አርሶ አደሮቹ ያስረዳሉ።

ከአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል አቶ እሸቱ ታደሰ ለመኸር እርሻ የሚውሉ የአፈር ማዳበርያ፣ ምርጥ ዘርና ፀረ-አረም ኬሚካል ከሎሜ አዳማ የገበሬዎች ኅብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን በብድር ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ዩኒየኑ ለአርሶ አደሩ ግብዓት በወቅቱ ማቅረቡ ከህገ-ወጥ ነጋዴዎች መጭበርበር መታደጉን ተናግረዋል፡፡

ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ዘመናዊ የእርሻ ትራክተር እና ኮምባይነርም ለገበሬዎች ማቅረቡን የሚነግሩን ደግሞ አቶ ተሾመ ብርሞ ናቸው፡፡

በአርሶ አደሩ በኩልም በክላስተር ተቀናጅቶና መሬቱን አዘጋጅቶ ዝናብ እስኪጥል እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የዩኒየኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ ካሳዬ ቸሩ ለኢዜአ እንዳስረዱት የግብርና ግብዓቶች ዋጋ መናርን ተከትሎ ለአርሶ አደሮች የብድር አቅርቦት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡

በዘንድሮው ዓመትም ዩኒየኑ በመሰረታዊ ማህበራት በኩል 393 ሺህ 959 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 14 ሺህ 848 ኩንታል ምርጥ ዘር እንዲሁም 9 ሺህ 270 ኩንታል የፀረ-አረምና ፀረ-ተባይ ኬሚካል ለተጠቃሚዎች ለማሰራጨት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ መስፍን ተሾመ በበኩላቸው በዞኑ ካሉት 5 ዩኒየኖች መካከል የሎሜ አዳማ የገበሬዎች ኅብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ለአርሶ አደሩ ማዳበርያ፣ የዘር ብዜት፣ ምርጥ ዘር ና የፀረ አረም ኬሚካል በብድር ማቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

የሎሜ አዳማ የገበሬዎች ኅብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን በ1989 ዓ.ም በ350 መስራች አባላት እና በ 150 ሺህ ብር የመመስረቻ ካፒታል በአንድ ወረዳ የተመሰረተ ሲሆን አሁን ተደራሽነቱን ወደ አራት ወረዳ በማስፋፋት በስሩ 63 ሺህ አባላትን ያቀፈ ነው።

የዩኒየኑ አጠቃላይ ካፒታል ከ79 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም