የኢትዮጵያ ህዝብ ተከባብሮና ተባብሮ ለአገሩ አንድነት እንዲተጋ ተጠየቀ

248

ሚያዝያ 12ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝብ ተከባብሮና ተባብሮ ለአገሩ አንድነትና ልማት መትጋት አለበት ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር እንድሪስ ጠየቁ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የረመዳንን ወር ምክንያት በማድረግ ለቋሚ ደምበኞች እና ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የኢፍጣር መርሐ ግብር አካሄደ።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር እንድሪስ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለመከባበርና ለመተባበር ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ሕዝቡ በዚህ ወቅት ሰላምና ልማት ላይ በማተኮር ኢትዮጵያን ለመለወጥ እንዲተጋ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የህዝበ ሙስሊሙ የዘመናት ጥያቄዎች መልስ እያገኙ መሆኑን የጠቀሱት ተቀዳሚ ሙፍቲ ይህ አካሄድ ተጠናክር ይቀጥላል ብለዋል።

አየር መንገዱ ቋሚ ደንበኞቹን እና አብረውት የሚሰሩ አካላትን አክብሮ ላደረገው መስተንግዶ ምሥጋናቸውንም አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፡ 'ከኢድ እስከ ኢድ' በሚል  አገራዊ ጥሪን ተቀበለው ለሚመጡ እንግዶች የተሻለ ዝግጅት ተደርጓል ይላሉ።

እስካሁንም አየር መንገዱ ወደ አገራቸው ለሚመጡ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች 20 በመቶ ቅናሽ አድርጎል ብለዋል።

አየር መንገዱ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በሀጂ እና ኡምራ ጉዞ የቆየ ትብብርና ደንበኝነት ያለው መሆኑን አስታውሰዋል::

በቀጣይም የሚሰጠውን ሃይማኖታዊ የጉዞ አገልግሎት አጠናክሮ ለማቀጠል ዝግጅቱን ያጠናቀቀ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በኢፍጣር ስነ-ስርዓቱ ላይ የአየር መንገዱ ስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የስራ ኃላፊዎች፣ የእስልምና እምነት ታላላቅ አባቶችና ተከታዮች እንዲሁም የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም