በሱማሌ ክልል የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ለህጻናት እየተሰጠ ነው

146

ጂግጂጋ፤ ሚያዚያ 11/2014(ኢዜአ) በሱማሌ ክልል ከአንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ ለሚበልጡ ሕጻናት የሚሰጥ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት በዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የህብተሰብ ጤና ድንገተኛ አስተዳደር  ዳይሬክተር አቶ አቡበከር ሼክ አደን ዛሬ  እንዳሉት፤ ለስድስት ቀናት የሚቆየው የክትባት ዘመቻው  በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች፣ መንደሮችና የስደተኞች መጠሊያ ጣቢያዎች ቤት ለቤት በመሰጠት ላይ ነው ፡፡

በዘመቻው እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሕጻናት እንደሚከተቡ ጠቅሰው፤ ስራውን የሚያካሂዱ አስራ ሁለት ሺህ ለሚጠጉ የጤና ባለሙያዎችና ሦስት ሺህ አራት መቶ በጎ ፈቃደኞች መሰማራታቸውን አስታውቀዋል፡፡  

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የፖሊዮ በሽታ መከላከያ የክትባት ዘመቻ ስኬታማነት ከቢሮው ጋር በመተባበር   የኢትዮጵያ የህብረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት(ዩኔሴፍ) እና የዓለም ጤና ድርጅት በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በክትባቱ ዙሪያ ለሃይማኖት መሪዎች ግንዛቤ የመስጠቱ ስራ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

የሱማሌ ክልል እስልምና ምክር ቤት ሊቀ መንበር ሼህ አህመድ አቢ ፤ ወላጆች ልጆቻቸው ከፖሊዮ በሽታ ለመጠበቅ  በወቅቱ እንዲያስከትቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በጅግጅጋ ከተማ ቀበሌ 05 ዞን ስምንት ነዋሪ ወይዝሮ ኡባሕ አህመድ አሊ በሰጡት አስተያየት "ክትባቱ ልጆቻችን ተላላፊ ከሆነው ከባድ የፖሊዮ በሽታ ይጠብቀዋል የሚል እምነት ስላላኝ ያለ ማቋረጥ አስከትባሉ “ ብለዋል። 

ባለፈው ህዳር ወር በተካሄዳው ተመሳሳይ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከአንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺህ በላይ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት ተጠቃሚ መሆናቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም