በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ ዞን በ76 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ ተግባራዊ ይደረጋል--ቢሮው

142

ባህርዳር ሚያዚያ 11/2014 ( ኢዜአ) ከግንቦት ወር 2014 ዓም ጀምሮ በ20 ሚሊዮን ብር በጀት በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ ዞን በሚገኙ 76 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተግባራዊ እንደሚደረግ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ከየካቲት 2014 ዓም  ጀምሮ በ248 ትምህርት ቤቶች  ከ98 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ተነግሯል ።

የቢሮው የስርዓተ ምግብ ባለሙያ አቶ ተዋበ ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት የምገባ ፕሮግራሙ የሚካሄደው  አሸባሪው ህወሓት ዘረፋና ውድመት በፈፀመባቸውና የምግብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ነው።

የምገባ ፕሮግራሙ መጀመር ተማሪዎች ትምህርታቸውን በንቃት እንዲከታተሉና የተማሪዎችን መጠነ ማቋራጥ ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት በመደበው 20 ሚሊዮን ብር በጀት ከመጪው ግንቦት ወር 2014 ዓም ጀምሮ በዋግኸምራ ብሄረሰብ ዞን በድሃናና ጋዝጊብላ ወረዳዎች በሚገኙ 76 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም እንደሚጀመር ተመላክተዋል።

እስከ ሐምሌ 2014 ዓ.ም በሚቆየው የምገባ ፕሮግራም ከአፀደ ህፃናት እስከ 8ኛ ክፍል የሚገኙ ከ27 ሺህ በላይ ተጨማሪ ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅት ለፕሮግራሙ የሚውል ከ3 ሺህ ኩንታል በላይ አልሚ ምግብ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከየካቲት 2014 ዓም ጀምሮ በክልሉ ሰሜንና ደቡብ ወሎ ፣በዋግኸምራና ኦሮሞ ብሄረሰብ  ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 248 ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ በሚገኘው የምገባ ፕሮግራም ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚማሩ 98 ሺህ 100 ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።

የምገባ ፕሮግራሙ "ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢዱኬሽን፣ በኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲብ ፣ ሴቭ ዘ ችልድረንና የዓለም ምግብ ድርጅቶች በተባሉ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንደሆነ ተገልጿል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ በየወሩ 2ሺህ 145 ኩንታል አልሚ ምግብ፣ 9ሺህ 711 ካርቶን ብስኩት፣ 46 ሺህ 200 ሊትር የምግብ ዘይትና ጨው እያቀረቡ መሆኑን አብራርተዋል።

"በትምህርት ቤቱ ምገባ መጀመሩ ተማሪዎች ስለ ምግብ ሳያስቡ ትምህርታቸውን ብቻ እንዲከታተሉ አግዟል "ያሉት ደግሞ በዋግኸምራ ዞን ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የወለህ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርት ብርቅ ወርቁ ናቸው።

"የምገባ ፕሮግራሙ ተማሪዎች በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ከደረሰባቸው የስነ ልቦና ችግር በመውጣት ተሳትፏቸው እንዲጨምር አቅም ፈጥሯል" ሲሉ ተናግረዋል።

በወለህ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ አፀደ ማሞ በትምህርት ቤቱ ምገባ መጀመር ስለ ምግብ ሳታስብ ትምህርቷን በአግባቡ እንድትከታተል እንዳገዛት ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም