የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም በጓሯችን አትክልት አልምተን መጠቀም ጀምረናል -ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች

183

አሶሳ ፤ ሚያዚያ 11 /2014(ኢዜአ) የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም በመኖሪያ ቤታቸው የጓሮ አትክልቶችን አልምተው መጠቀም መጀመራቸውን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች ተናገሩ።

“ምግባችንን ከጓሯችን፤ ጤናችንን ከምግባችን"  በሚል መሪ ሀሳብ  የብልጽግና ፓርቲ  የክልሉ ሴቶች ሊግ አባላት  ዛሬ በአሶሳ ከተማ የንቅናቄ መድረክ አካሄደዋል፡፡

ከተሳታፊዎቹ  መካከል ወይዘሮ ሃቢባ ያህያ በሰጡት አስተያየት ፤ እየተባባሰ ለመጣው የኑሮ ውድነት መንግስት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡም የራሱን መፍትሔ መፈለግ የግድ ይላል ነው ያሉት።

የወዳደቁ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን እና የማዳበሪያ ከረጢቶችንን ተጠቅሜ በጓሮዬ በትንሽ ቦታ ላይ አትክልት ማምረት ጀምሬያለሁ ያሉት ወይዘሮ ሃቢባ፤ ጎመንን ጨምሮ ያመረቷቸው የተለያዩ  አትክልቶች  መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የከተማ ግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት አልምቼ ተጠቃሚ የመሆን እቅድ ስላለኝ እቀጥላለሁ ብለዋል አስተያየት ሰጪዋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፡፡

ከመተከል ዞን  የመጡት ወይዘሮ ነገሬ ፉፋ በበኩላቸው፤ በጸጥታ ችግር ውስጥ ሆነን ራሳችንን በምግብ ለመቻል የድርሻችንን ወስደን ጥረት እያደረግን ነው  ብለዋል፡፡

ያላቸውን 300 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ በሚገባ በጓሮ አትክልት እና ፍራፍሬ እንዳለሙበት ጠቅሰዋል፡፡

ስራውን በማህበር ተደራጅተው እንደሚያካሂዱት ጠቁመው፤ የበጋ ወቅትን የውሃ እጥረት ችግርን ለመፍታት በአማራጭነት  የጉድጓድ ውሃ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፡፡

ተሞክሯችንን ለሌሎች ሴቶች እያከፈልን ነው ሲሉ አስረድተዋል ወይዘሮ ነገሬ፡፡

ወይዘሮ አበራሽ ደጃስ በበኩላቸው ፤ በኑሮ ውድነቱ ዋነኛ ተጠቂ ሴቶች ናቸው ይላሉ፡፡

ክልሉ ሰፊ ለም መሬት ያላው በመሆኑ  ሴቶች ደግሞ በጉልበት ስራ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ቢሆንም አቀናጅተን በመስራት የሊጉ አባላት ብዙ ይጠብቀናል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ በክልሉ  አካባቢዎች የሚመረቱ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ሰብል የዋጋ ንረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ህገወጥ ደላሎችን ማስቆም ሌላው ስራችን ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  ሴቶች ሊግ ጽሀፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ከልቱም ባበክር፤  በክልሉ በመኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ የተጀመረው የግብርና ልማት ስራዎች ቢኖሩም ተጠናክረው ሳይቀጥሉ መቅረታቸውን አስታውሰዋል፡፡

የንቅናቄ መድረኩ  ዓላማ በፓርቲው አንደኛ መደበኛ ጉባኤ የተቀመጡ ሃገራዊ ቅጣጫዎች መሠረት በማድረግ የከተማ ግብርና አጠናክሮ ማስቀጠል ነው ብለዋል፡፡

የሊጉ አባላት በየአካባቢው ያገኙትን ተሞክሮ ለማስፋት ጽሕፈት ቤቱ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አመልከተዋል፡፡

ይህንኑ መሠረት በማድረግ በቀጣይ ወራት 60 ሺህ ሴቶችን በመኖሪያ ግቢ ውስጥ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ሌሎች ልማቶች በማሳተፍ ቤተሰቦቻቸው የኑሮ ውድነቱን እንዲቋቋሙ ለማድረግ አቅደናል ብለዋል፡፡

 የግብርና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ የሚሰጡበት ሁኔታም እንደሚመቻች ሃላፊዋ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በንቅናቄው መድረክ ከ500 በላይ በክልሉ  የሴቶች ሊግ አባላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም