ቡናን ከሌሎች ምርቶች ጋር በስብጥር በማልማት የምግብ ዋስትና ችግርን ለመፍታት ሊሰራ ይገባል- ቋሚ ኮሚቴው

108

ዲላ፤ ሚያዝያ 11/2014)ኢዜአ) ቡናን ከሌሎች ምርቶች ጋር በስብጥር በማልማት የምግብ ዋስትና ችግርን ለመፍታት ሊሰራ እንደሚገባ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው በደቡብ ክልል በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ በምችሌ ሲሶታ ቀበሌ በአርሶ አደሮች ማሳ እና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዲላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በመገኘት በቡና ልማትና ግብይት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ተመልክቷል፡፡

 በዚህ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ጸሐፊ አቶ መለሰ መና እንዳሉት፤ የምርምር ተቋማት ከአርሶ አደሩና ከሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች  ጋር በመሆን የቡና ምርታማነትን ለማሻሻልና ግብይቱን ለማዘመን ያከናወኑት ተግባር ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡

በተለይ አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም በማደራጀት ከተለመደው አሰራር እንዲወጡ ከማድረግ በተጓዳኝ ምርታማነታቸው የተረጋገጡ የተሻሻሉ የቡና ዝሪያዎችን እንዲያለሙ መደረጉ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

በቡና ልማቱ የተጀመሩ የኩታ ገጠም፣ የቡና እደሳት ስራዎችንና አዳዲስ የአሰራር ዘዴዎችን ከማስፋት ጎን ለጎን በቡና ማሳ ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ቡናን ከሌሎች ምርቶች ጋር በተለይ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ከቅመማ ቅመምና ስራስር ምርቶች ጋር በስብጥር በማልማት የምግብ ዋስትና ችግርን ለመፍታት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የቡና ግብይት የውጪ ምንዛሪ ከማምጣት አንጻር የተሻለ ለውጥ ቢታይበትም ቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች የሃላፊነትና ተጠያቂነት ወሰን ሊበጅላቸው  እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አርሶ አደሮች ከቡና የሚያገኙት ገቢ ማደግ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጅን በአጭር ጊዜ ለመላማድ ተነሳሽነት የሚፈጥር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ክልል ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ አማኑኤል ብሩ ናቸው።

በክልሉ ጥራት ያለው ቡና ለገበያ በማቅረብ፣  የላኪና አቅራቢዎችን ትስስር በማጠናከር አርሶ አደሩ በተሻለ ዋጋ ሸጦ የልፋቱን ዋጋ እንዲያገኝ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

ዘንድሮም ቀጥታ ትስስር ግብይትን በመጠቀም ምርት ያዘጋጁ 424 አርሶ አደሮች ቡናቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጌዴኦ ዞን  ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ በበኩላቸው፤ በአርሶ አደሮች ማሳ ቡናን በኩታ ገጠም የማልማት ጅምር ስራ ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ የማስፋት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል

ከዞኑ በየዓመቱ በአማካይ ከ25 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብ ጠቅሰው፤  ዘንድሮም በተሻለ ጥራት ከ29 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ህግ ወጥ የቡና ዝውውርንም ለመከላከል  በተደረገ ጥረት ከ3ነጥብ 6 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ቡና  መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም