ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የኮንትሮባድ ሲጋራ ተያዘ

154

ሐረር ሚያዝያ 11/2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጎሮ ጉቱ ወረዳ ግምቱ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ሲጋራ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ ለኢዜአ እንደገለጹት ሲጋራው ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በጎሮጉቱ ወረዳ በጸጥታ ሀይሎች ትብብር ትናንት ሌሊት ተይዟል።

ሲጋራው የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3- 25459 ኦሮ በሆነ ተሽከርካሪ ተጭኖ ከሶማሌ ክልል ቢኬ ከተማ ወደ ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቦረዳ ከተማ ሊገባ ሲል መያዙን ተናግረዋል።የተያዘው ሲጋራ ለጉምሩክ ኮሚሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።

ሲጋራውን ሲያጓጉዝ የነበረው አሽከርካሪ ለጊዜው በመሰወሩ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን አመልክተዋል

በዞኑ ኅብረተሰቡ ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግድን በመቆጣጠር ሂደት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ኃላፊው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም