የፌደራሉና የክልል መንግስታት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋምና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል

87

ሚያዚያ 11/2014(ኢዜአ)  የፌደራሉና የክልል መንግስታት በአማራና በአፋር ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋምና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጠየቀ።

ተቋሙ በአማራና አፋር ክልሎች በሚገኙ አካባቢዎች በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረግ ሰብዓዊ ድጋፍ፣ መሰረታዊ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥና መልሶ የማቋቋም ሥራ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ያካሄደውን የዳሰሳዊ ቁጥጥር ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

የዳሰሳ ቁጥጥሩ የተካሄደው በአማራ ክልል ሰባት ዞኖችና በአፋር ክልል ሁለት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ከመጋቢት 14 እስከ ሚያዚያ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ነው ተብሏል።

በዚህም መሰረት ተቋሙ አራት ቡድኖችን በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደርና በዋግኸምራ ዞኖች እንዲሁም በአፋር ሃውሲና ፈንቲ ዞኖች በማሰማራት የዳሰሳ ቁጥጥር ማካሄዱ ተገልጿል።

በዞኖቹ በመጠለያ ካምፕ የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ የጦርነቱ ሰለባዎች፣ መሰረታዊ የመንግሥት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ውድመት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና ሌሎችም የግልና የመንግሥት ንብረቶች ላይ ምልከታ ማካሄዱን ተጠቅሷል።

በተቋሙ የሴቶች፣ ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ጉዳይ ዳይሬክተር ሰብለወርቅ ታሪኩ፤  በአማራ ክልል ከጦርነቱ ማግስት የተፈናቀሉ ዜጎችና የወደሙ መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በመንግሥትና ሌሎች አጋር አካላት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሯ ለተጎጂዎች ሰብዓዊ እርዳታዎችን የማድረስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ በቂ አለመሆንና የፍትሃዊነት ጥያቄ እየተነሳበት መሆኑን በተካሄደው የዳሰሳ ቁጥጥር ተረጋግጧል ነው ያሉት።

በአፋር ክልል የተሰማራውን የቁጥጥር ቡድን ሪፖርት ያቀረቡት የተቋሙ የአስተዳደራዊ በደል መከላከል ዳይሬክተር አዳነ በላይ፤ ልዩ ትኩረት ለሚሹ የኅብረተሰቡ ክፍሎች በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ነው ያብራሩት።

በጦርነቱ የተጎዱ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በከፊል ጥገና ተደርጎላቸው፤ ወደ አገልግሎት እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን በዳሰሳ ቁጥጥሩ መመልከት መቻሉን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ዳሰሳ ከተደረገባቸው ዞኖች ውስጥ በተወሰኑ አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በጸጥታ ሥጋት ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑ ጠቅሷል።

በመሆኑም መንግሥት በዞኖቹ አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታን የማስፈን ተግባር እንዲያከናውን ጠይቋል።

በመግለጫው የጤና ሚኒስቴርና የትምህርት ሚኒስቴር የፌደራል ተቋማትን በጦርነቱ ከተጎዱ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ወደ መልሶ ግንባታ የሄዱበት እርምጃ በበጎ ተጠቅሷል።

ሆኖም የመልሶ መቋቋም እንቅስቃሴው በፌደራልና በክልል ደረጃ በእቅድና በበጀት የተደገፈ ምላሽ እየተሰጠው አለመሆኑ፣ የመንግሥት ተቋማትና የልማት ድርጅቶችም ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ አለመመለሳቸው አሳሳቢ መሆኑ በዳሰሳው መረጋገጡ ተጠቅሷል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በክልልና በተዋረድ በሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች የደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መደበኛ ጥራት ያለውና የተሟላ የመንግሥት አገልግሎት ለመስጠትና ለማስቀጠል የሚያስችል እንዳልሆነ በዳሰሳ ቁጥጥር ሪፖርቱ ተጠቅሷል።

ለአገልግሎት አሰጣጥ ችግርና ለመልካም አስተዳደር እጦት የሚያጋልጡ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን በፍጥነት ለማሳካት የፌደራል መንግስቱ፣ ክልሎችና በየደረጃው የሚገኙ አስተዳደሮች በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባቸው ጠቁሟል።

በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውና ከኅብረተሰቡ የዕለት ተለት እንቅስቃሴና መረጃ ጋር የሚያያዙ የማዘጋጃ ቤታዊ፣ የፍትህ፣ የጸጥታ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም ሌሎች ተቋማትን በአፋጣኝ ወደ አገልግሎት እንዲገቡም ጠይቀዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በሪፖርቱ የተለዩ ችግሮች በፍጥነት እንዲታረሙ አስፈጻሚው አካል ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም