የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያን በአማራጭነት ለመጠቀም የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ እቅድ ወጥቶ እየተሰራ ነው

171

ሚያዝያ 11 2014 (ኢዜአ) የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያን በአማራጭነት ለመጠቀም የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ እቅድ ወጥቶ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ አያያዝ እና አጠቃቀምን በተመለከተ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ፤ በዓለም ነባራዊ ሁኔታ ሰው ሰራሸ የኬሚካል ማዳበሪያ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡

የማዳበሪያ መሸጫ ዋጋ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ሙሉ ለሙሉ  የዋጋ መናር የታየበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፍ የማዳበሪያ ዋጋ ማሻቀብ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ፕሮፌሰር እያሱ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ኬሚካል የአፈር ማዳበሪያን ሙሉ በሙሉ ከውጭ  የምታስገባ ስለሆነ በዋጋ ጭማሪው ሳቢያ በአቅርቦቱ ላይ እጥረት ማስከተሉን ጠቅሰዋል።

የውጫዊ ጫናዎችም መበራከት ለማዳበሪያ አቅርቦት ጉድለት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያን በአማራጭነት እንዲጠቀሙ ለማድረግ ሚኒስቴሩ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር  ተፈራ ሰለሞን፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጋር ደባልቆ መጠቀም ምርታማነትን የሚያሳድግ መሆኑን አስረድተዋል።

የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ጥገኝነት ሊያላቅቅ የሚችል የሃገር ሀብት በመሆኑ በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።

የግብርና ባለሙያዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያን አርሶ አደሮች በአማራጭነት እንዲጠቀሙ ለማስቻል ሥልጠና እየተሰጣቸው ይገኛል።

በኢትዮጵያ ለተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ ሃብቶች ቢኖሩም በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንዳልሆነ ይነገራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም