በአዲሱ ዓመት የበጎ አድራጎት ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን- ነዋሪዎች

94
ጳጉሜን 1/2010 የሃገሪቱን ለውጥ ተከትሎ እየተነቃቃ ያለውን የበጎ አድራጎት ስራ በአዲሱ ዓመትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ ፡፡ መጪው አዲስ ዓመት እስካሁን ካሳለፏቸው በዓላት በተለየ ፍቅር ፣ ነፃነትና አንድነት የሰፈነበት እንደሚሆን ተስፋ በመሰነቅ በደስታ ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡ የድል በትግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የበጎ ፍቃድ ክበብ አስተባባሪዋ መምህርት እንዳለች ሀይሌ እንዳለችው የበጎ አድራጎት ስራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባሳዩት አርዓያነት ተማሪዎች በትምህርት መሳሪያ ችግር  ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ከአምናው በተሻለ ከተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡ ከእናት ወግ ፣ ከድርጅቶችና ከመምህራን መዋጮ በትምህርት ቤቱ ሲካሄድ የቆየው የምገባ ፕሮግራምም በቀጣዩ ዓመት 250 ተማሪዎችን በመጨመር 600 ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መምህሯ ተናግራለች፡፡ “በጎስራ ከመስራት የበለጠ  ህሊናን  የሚያስደስት ነገር የለም” ያለችው  መምህርት እንዳለች አንድን ህፃን አስተምሮ ለቁምነገር ማብቃት ሀገራዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደሆነ አስታውቃለች፡፡ በቀጣዩ አዲስ ዓመት መምህራንን በማነሳሳትና አጋዥ መፅሃፍትን በእጣ በማቅረብ፣በሙዚቃና በስእል ስራዎች ተማሪዎች ችሎታቸውን እንዲያዳብሩና በተጓዳኝ የሚገኙ ገቢዎችን ለበጎ ስራ ለማዋል እንሰራለን ነው ያለችው ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ”በጎ ስራን ከጎረቤት መጀመር” በሚል ያሳዩትን አርአያነት በመከተል አዲሱን ዓመት በጎ ስራ በማከናወን እንደምትቀበለው የገለጸችው ደግሞ በንግድ ስራ የተሰማራችው ወጣት ሰላም በየነ ናት፡፡ በንግድ አካባቢያቸው ያሉ ተማሪዎችን በጋራ የትምህርት መሳሪያ በመግዛት የመስጠት ልምዳቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፃለች ፡፡ ወቅት እየጠበቁ የሚደረጉ እገዛዎች የልጆቹን ጊዜያዊ ችግር እንጂ በዘላቂነት ህይወታቸውን የሚቀይር ባለመሆኑ በቋሚነት እገዛ የሚደረግባቸው ማዕከላት ሊጠናከሩ እንደሚገባም ወጣት ሰላም አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡ "በሃገሪቱ የመጣው ለውጥ ያስገኘውን ነፃነት በአግባቡ በመጠቀም ሩቅ ሳናይ አጠገባችን ባለው ነገር እራሳችንን ለመቀየር እንሞክር፤ከተሰራና ከተለፋ የማይቀየር ነገር የለም ”ስትል የአዲስ ዓመት መልእክቷን አስተላልፋለች፡፡ “አዲሱን ዓመት ባለው መነቃቃት በአዲስ ራእይ ለመቀበልና ለማክበር ተዘጋጅቻለሁ” ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጭ አቶ ክብረት ካሳዬ ናቸው፡፡ “አምና በዚህ ሰአት የሃገሪቱ ሁኔታ የተመሰቃቀለበት በመሆኑ ለበአል ወደ ቤተሰብ ስሄድ በሰላም ለመግባት ጥርጣሬ ነበረኝ” ያሉት  አቶ ክብረት ዘንድሮ ሙሉ ለሙሉ ከጥርጣሬ  ወጥተው ወደ ሙሉ ተስፋና አዲስ መንፈስ በመሸጋገር በአሉን ለማክበር መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በአገሪቱ እየተነቃቁ ያሉ በጎ ስራዎች በመዲነዋ ሳይወሰኑ በመላው ሃገሪቱ መስፋፋት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ በእረፍት ጊዜያቸው በጎረቤት ያሉ ልጆችን በማስጠናትና እንዴት ቢያጠኑ ምን ቢያነቡ ውጤታማ እንደሚሆኑ ምክር በመለገስ እንደሚያሳልፉና ወደ ፊት አቅመ ዳካሞችን የማገዝ ፍላጎት እንዳላቸውም አስታውቀዋል፡፡ ሌላው የመዲናዋ ነዋሪ ወጣት ወንድአፍራሽ ወልዴ እንዳለው እያጠናቀቅን ያለው ዓመት  ብዙ ችግሮች የተፈቱበትና ለውጦች የታዩበት ነው ፡፡ "አምና በዚህ ጊዜ ተስፋ ያጣንበት፣እርስበእርስ የማንተማመንበት፣ጓደኞች የምንፈራራበትና የምንፈራረጅበት" ጊዜ ነበር ያለው ወጣቱ አሁን ላይ "ነፃነት አግኝተን፣ተደምረን አንድ የሆንበት ጊዜ በመሆኑ መጭውን አዲስ አመት በደስታ ለማሳለፍ ተዘጋጅቻለሁ" ነው ያለው ፡፡ በሃገሪቱ ያሉ ለውጦች ለስራ የሚያነሳሱና የሚያተጉ በመሆናቸው «ከነበረኝ አቅም ጨምሬ  የተሰጠኝን ስራ  በትጋትና በኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ » ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም