ኢዜአ የ80 ዓመት ጉዞውን በማስመልከት በሀዋሳ ከተማ ለህዝብ እይታ የከፈተው አውደርዕይ ተጠናቀቀ

162

ሀዋሳ፣ ሚያዚያ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ ላለፉት ሶስት ቀናት ለህዝብ ክፍት የተደረገው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የ80 ዓመት ጉዞውን የሚያስቃኝ የፎቶና የቪዲዮ አውደርዕይ ዛሬ ተጠናቀቀ።

በአውደ ርዕዩ የታደሙ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት የኢዜአ የረዥም ጊዜ ልምድ ለመገናኛ ብዙሀን ዘርፍ እድገት አስተዋዕኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ተሳታፊዎቹ በቀጣይም  ከተቋሙ ጋር በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች አብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ዐውደ ርዕዩን ከጎበኙት መካከል የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አፈወርቅ አለማየሁ ኢዜአ በሀገሪቱ ቀዳሚ ከሚባሉ ተቋማት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአውደ ርእዩ የተመለከቷቸው ሁነቶችም ተቋሙ ወሳኝና ወቅታዊ የሆኑ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ ቀዳሚ መሆኑን የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ተቋሙ በሃገሪቱ የሚካሄውን ለውጥ በመደገፍ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ የሚከናወኑ የልማትና የለውጥ ስራዎች ለህዝቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ከተቋሙ ጋር የሚሰሩ  ስራዎችን ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል ፡፡

ኢዜአ በቀጣይም በክልሉ የሚከናወኑ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ህዝብን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ የዘገባ ስራውን እንዲያከናውን ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል ፡፡

"ተቋሙ በተለይም  በአፍርካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማስጠበቅ ሊሰራ ያቀዳቸው ተግባራት ን እንዲያሳካ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል" ብለዋል  ፡፡

በእውነት ላይ የተመሰረቱ ዘገባዎች ለክልሉ እድገትና ሰላም ጠቃሚ መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ አውደ ርዕዩን የተመለከቱት በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ሃላፊ አቶ አስፋው ጎኒሶ ናቸው።

ተቋሙ በዚህ ረገድ ተጠቃሽና ረዥም ልምድ ያለው መሆኑን በመግለጽ በክልሉ በተለያየ ዘርፍ በሚከናውኑ ተግባራት በጥንካሬም ሆነ መታረም በሚገባቸው ጉድለቶችን  በማሳወቅ  በኩል   ከተቋሙ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

ኢዜአ ላለፉት 80 ዓመታት የህዝብ አፍና ጆሮ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱን ጠቅሰው "ተቋሙ በአፍሪካ ቀዳሚ የዜና ምንጭ ለመሆን የያዘውን እቅድ ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል ፡፡

በሀዋሳ የተካሄደው የኢዜአን 80 ዓመታት ጉዞ የሚያሳይ አውደ ርዕይ  በሲዳማና ደቡብ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎች  እንዲሁም  በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጎብኝቷል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም