የተሻሻለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ምክር ቤቱ የስራ ዘመን እንደተከፈተ ይቀርባል ተባለ

177
አዲስ አበባ ጳጉሜ 1/2010 የተሻሻለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ በአዲሱ ዓመት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሳምንታት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ያዋቀረው የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት ለኢዜአ እንደገለጸው፤ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅን ለማሻሻል የተሰማራው አጥኝ ቡድን ረቂቅ አዋጁን አጠናቋል። በመሆኑም የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ በሚመለከታቸው አካላት በኩል አስፈላጊው የማጎልበት ተግባራትን ካለፈ በኋላ በአዲሱ ዓመት የፓርላማው መክፈቻ ቀዳሚ ሳምንታት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል። ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በሥራ ላይ የሚገኘው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ የሰብዓዊ መብት ጥበቃንና የዴሞክራሲ ባህል መቀጨጭን ጨምሮ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕግና ፍትሕ ስርዓት መጥበብ የራሱ የሆነ አሉታዊ ሚና እንደነበረው የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አዋጁ አገሪቱ ትመራበታለች ከሚባለው "የህገ-መንግስት ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭ፤ ፀረ ህገ- መንግስታዊና የሚመለከታቸው ወገኖች በወጉ ያልመከሩበት ነው" ሲሉም ይተቻሉ። የጥብቅናና የህግ ጉዳይ አማካሪው አቶ ወንድሙ ኢብሳ አዋጁ "ከምርጫ 97 ማግስት ህዝብ በገዢው ፓርቲ ላይ ያሳየውን ቁጣ ለማዳፈን እንደ ጸረ-ሽብር ሕጉ፤ የሕግ ስርዓቱን ሳያጋናዝብ የወጣ አፋኝ አዋጅ ነው" ይላሉ። በአማካሪ ምክር ቤቱ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ አጥኝ ንዑስ ኮሚቴ አባልና በጉዳዩ ላይ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው አቶ ቁምላቸው ዳኘ፤ በጎ አድራጎትና ሲቪክ ማህበራት የመደራጀት መብት በተመለከተ በፍትሐ ብሔር ሕግ እንጂ የራሱ የሕግ ማዕቀፍ እንዳልነበረው ያወሳሉ። ስለሆነም ድርጅቶችንና ማህበራትን የሚዳኝ አዋጅ መውጣቱ በመልካም ጎን የሚታይ እንደሆነ ገልጸው፤ ይሁንና በ2001ዓ.ም የወጣው አዋጅ አስፈላጊው ውይይት ያልተደረገበት፣ የመንግስትን ፍላጎት ብቻ በህዝብ ላይ ለመጫን የወጣ እንጂ አማራጭ ሃሳቦች ያልቀረበበት እንደነበርም ያነሳሉ። አዋጁ የድርጅቶችን የመደራጀት መብት ለማረጋገጥ የማያስችል በመሆኑ፣ በተቋቋሙት ድርጅቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በተለይም በማኅበራት አገልግሎት በሚያገኙ የህብረሰተብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ያስታውሳሉ። በተለይም በሴቶች፣ ህጻናትና አካል ጉዳተኞች ላይ ጉዳቱ ከፍተኛ እንደነበር በመጥቀስ። በተለይም በሰብዓዊ መብቶች ላይ ሲሰሩ የነበሩ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በአዋጁ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ምክንያት መጠናከር ተስኗቸው የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ተግባራቸው እንዲገታ በመደረጉ የአገሪቱ ዴሞክራሲ ባህል እንዲቀጭጭ ተጽዕኖ ፈጥሯል። ለአብነትም የኢትዮጵያ ሴቶች የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ከ15 እስከ 20 ሺህ ለሚደርሱ ሴቶች ነጻ የሕግ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ቢሆንም፤ አዋጁ ከወጣ ከሶሰት ዓመታት በኋላ ግን ማህበሩ በዓመት የሚሰጠው የሕግ አገልግሎት ከ5 ሺህ ሴቶች አለመብለጡን ነው አቶ ቁምላቸው ያነሱት። አዋጁ የተቋቋሙትን ማኅበራትና ድርጅቶች ከማዳከም ባሻገር ወደፊት ሌሎች እንዳይፈጠሩም ምክንያት ሆኗል ሲሉም ገልፀዋል። ሀሳብ በነጻነት የሚንሸራሸርባቸው መድረኮች መጥፋታቸውም ላለፉት ሶስት ዓመታት በአገሪቱ ለተፈጠረው አመጽና ሁከት አንዱ ምክንያት ሆኖ ሊጠቀስ እንደሚችልም ተናግረዋል። 'ቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ' የተባለ የግብረ ሰናይ ድርጀት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደለ ደርሰህ በበኩላቸው፣ የአዋጁ መሻሻል ለረጅም ጊዜ ሲጎተጉቱ መቆየታቸውን ገልጸው፤ አዋጁን ለማሻሻል የተጀመረውን ሙከራ አድንቀዋል። "ልማት ዘላቂ የሚሆነው መብት ተኮር ስራ ሲሰራ ነው፤ ነገር ግን በአዋጁ ከተደነገጉ ጉዳዮች መካከል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ገቢ ከአስር በመቶ በላይ ከውጭ ድርጅቶች ድጋፍ እንዳይሆን ይከለክላል፤ ይህ ደግሞ በድሃ አገር ላይ ዘላቂ ልማት ለማምጣት አዳጋች ነው፤" ሲሉ አቶ ታደለ ገልፀዋል። ሥራው በሂደት ላይ የሚገኘው የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅም የሲቪክ ማህበራት የተጣለባቸውን አገራዊ ሚና በአግባቡና በነጻነት እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። በቅርብ ጊዜያት የተጀመረው የማሻሻያ አዋጁ አጥኚ ቡድን አባል አቶ ቁምላቸው አክለው እንደሚሉት፤ እስካሁን አዋጁ ከሕገ መንግስቱ፣ ከአፍሪካ የሰዎችና ሰብዓዊ መብቶች እነደዚሁም ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች አኳያ ያለውን ድክመትም አጥንቷል። ልምድ ያካበቱ የህግ ባለሙያዎችን ያካተተው ንዑስ ኮሚቴው በጥናቱ ላይ በመመስረት በጉዳዩ ላይ የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችና ስታንዳርዶችን አካቶ ረቂቅ ሕግ አዘጋጅቷል። በረቂቅ አዋጁ ላይም ውይይት መጀመሩን ያነሱት አቶ ቁምላቸው፤ በቀጣይም በፌዴራልና ክልሎች ከሚመለከታቸው ድርጅቶችና ማኅበራት ጋር ምክክር ተደርጎ አስተያየት ተሰባስቦበት በመጨረሻ ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ ይቀርባል። በጥናቱ ከ50 በላይ አንቀጾች በድክመት የተለዩ ሲሆን አስፈላጊው ግብዓትና ማሻሻያ ተደርጎበት ረቂቅ አዋጁ የመደራጀት መብትን ያረጋገጠ፣ ቀልጣፋ የምዝገባ ስርዓት፣ ደረጃውን የጠበቀ ገደቦች ያሉት፣ አስፈላጊ የራስ በራስ አስገዳጅ ቁጥጥርና ተጠያቂነት ባሟላ መልኩ የሚዘጋጅ ነው ብለዋል። እንደ አቶ ቁምላቸው ገላጻ እስከ መስከረም መጨረሻ የመጨረሻው ረቂቅ የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ያለው ቀጣይ ሂደት ተጠናቆ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመኑን በሚከፍትበት ሳምንት ባለው ጊዜ ውሰጥ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ረቂቅ አዋጅ 'የሲቪክ ማኅበራት አዋጅ' በሚል ስያሜ እንደሚሻሻልም ተገልጿል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም