የፆም ወቅትን በጦርነትና ተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በማገዝ ማሳለፍ ይገባል - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

365

ሚያዚያ 9/2014/ኢዜአ/  የፆም ወቅትን ራስን ለፈጣሪ ተገዥ በማድረግ በጦርነትና ተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችን በማገዝ ማሳለፍ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ።

ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በታላቁ ቤተ-መንግስት የኢፍጣር መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

በመርሃ-ግብሩ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ፣ የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ጀይላኒ ከድር፣ የእምነቱ ታላላቅ አባቶችና ተከታዮች ተገኝተዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በታላቁ ቤተ-መንግስት የተካሄደው የኢፍጣር መርሃ ግብር የኢትዮጵያዊያንን አብሮነትና መከባበር የሚያሳይ ነው፡፡

ወቅቱ የሁለቱ ታላላቅ እምነቶች ፆም የተገጣጠመበት መሆኑን እንደ መልካም አጋጣሚ በማንሳት፤ ይህም አማኙን ለፈጣሪው ተገዥ በማድረግ መልካም ተግባር እንዲፈጽም ይረዳዋል ብለዋል።

የፆም ወቅትን ከምግብ እራስን ማቀብ ብቻ ሳይሆን የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍና ያለንን  በማካፈል ማሳለፍ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመሆኑም ወቅቱን በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን በማገዝ ማሳለፍ እንደሚገባ ነው ፕሬዝዳንቷ ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የረመዳን ፆምን እያሳለፉ ለሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ፆሙ በሰላም እንዲጠናቀቅ በመመኘት ለኢድ አልፈጥር በዓል በሰላምና በጤና እንዲያደርሳቸውም መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ፤ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ለህዝበ ሙስሊሙ አክብሮታቸውን ለማሳየት የኢፍጣር መርሃ-ግብር በታላቁ ቤተ-መንግስት እንዲዘጋጅ በማድረጋቸው ምስጋና አቅርበዋል።

ከዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዲህ አይነቱን መርሃ-ግብር በቤተ-መንግስት ማካሄድ ፈጽሞ የማይታሰብ እንደነበር አስታውሰው፤ ከዚህ አኳያ የዛሬው የኢፍጣር መርሃ ግብር እጅግ አስደናቂ  ነው ብለዋል።

በመንግስት በኩል እየተፈጠረ የመጣውን የኃይማኖት አክብሮትና እኩልነት በመገንዘብም እድሉን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የረመዳን ወርን አስመልክቶ በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ባቀረቡት ከ"ኢድ እስከ ኢድ" ጥሪ መሰረት የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በሀገራቸው እንዲያከብሩ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም