ባለፉት ዘጠኝ ወራት የህግ ጥሰት በፈጸሙ 15 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል

443

ሚያዚያ 9/2014/ኢዜአ/ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የህግ ጥሰት በፈጸሙ 15 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት የህግ ጥሰት በፈጸሙ በአጠቃላይ 40 ተቋማት ላይ እስከመዝጋት የደረሰ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ነው ያለው፡፡

እርምጃ ከተወሰደባቸው 15 ተቋማት መካከል ሁለቱ ምንም ዓይነት እውቅና የሌላቸው ሆነው ተገኝተዋል።

የባለስልጣኑ እውቅና ፈቃድ አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ ዐቢይ ደባይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከመደበኛ ክትትል ባሻገር በ30 ተቋማት ላይ ድንገተኛ ፍተሻ በማካሄድ ህገወጥ ድርጊትን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በዚህም ተቋማዊ እውቅናና እድሳት ሳያገኙ ማስተማር፣ ያልተፈቀደላቸውን የትምህርት መስክ ማስተማር፣ እውቅና የሌላቸውን ቅርንጫፍ ኮሌጆች መክፈት የመሳሰሉ ህገ-ወጥ ተግባራት ስለመኖራቸው መረጋገጡን አንስተዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ በበኩላቸው፤ ባለስልጣኑ ከሁለት ዓመት በፊት የህግ ጥሰት የፈጸሙ 25 ተቋማትን መዝጋቱን አስታውሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ ህጋዊ እውቅና የሌላቸውን ጨምሮ የህግ ጥሰት በፈጸሙ 15 ተቋማት ላይ እስከ መዝጋት የደረሰ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት።

በዚህ ሳምንት ብቻ ሳይፈቀድላቸው የተለያዩ የትምህርት መስኮችን ሲያስተምሩ የተገኙ ተቋማት ላይ የማስተካከያና የእግድ እርምጃ መወሰዱንም አብራርተዋል፡፡

ህጋዊ እርምጃውን ተከትሎ የተወሰኑትን ተቋማት በወንጀል በመክሰስ እንዲቀጡ መደረጉንና ጉዳያቸው በክስ ሂደት ላይ የሚገኙ መኖራቸውንም ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ በሀገሪቱ የነበረውን የሰላምና ፀጥታ ችግር ተከትሎ፤ ያለምንም ህጋዊ ሰውነት ህንጻ ተከራይተው ተማሪዎችን በገፍ የሚያስመርቁ ኮሌጆች ተበራክተዋል ነው ያሉት።

ይህ ክስተትም የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ጭምር ያለምንም ህጋዊ ፈቃድ ሙሉ ህንፃ ተከራይተው ቅርንጫፍ ካምፓስ በመክፈት ሲያስተምሩ ተገኝተው እስከ አራት ካምፓስ የተዘጋባቸው ተቋማት አሉ ነው ያሉት።

ሌሎችም በባለስልጣኑ ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙ ተቋማት መኖራቸውን በመጥቀስ፤ የሚወሰድባቸው እርምጃ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ ይሆናል ብለዋል።

ባለስልጣኑ ክትትሉን አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ህብረተሰቡ በህገወጥ ተቋማት ተመዝግቦ ጊዜውንና ገንዘቡን ከማባከን እንዲቆጠብ አሳስበዋል።

ያለእውቅና ፈቃድ የሚያስተምሩ ተቋማትን ለባለስልጣኑ በመጠቆም የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም