ኢትዮጵያን በታዳጊዎች እግር ኳስ በአፍሪካ ዋንጫ ለማሳተፍ ግብ ተቀምጦ እየተሠራ ነው

487

አሶሳ ፤ ሚያዚያ 8/ 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ከአራት ዓመት በኋላ በታዳጊዎች እግር ኳስ በአፍሪካ ዋንጫ ለማሳተፍ ግብ ተቀምጦ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሪሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተናገሩ፡፡

በአሶሳ ከተማ ለሚገኙ ከ20 ዓመት በታች የታዳጊዎች እግር ኳስ ፕሮጀክት ሰልጣኞች ፌዴሬሽኑ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በሁለቱም ፆታ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ወጣቶች በ" ፓይለት"  እግር ኳስ ፕሮጀክት ታቅፈው ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡

አቶ ኢሳያስ እንዳመለከቱት፤ ስልጠናው ከዓለም አቀፍ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል(ፊፋ) ከአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን(ካፍ) በመጡ ባለሙያዎች ጭምር የታገዘ እየተሰጠ ነው።

“አንድ ኳስ ለአንድ ሰልጣኝ” በሚል መርህ የስፖርት ቁሳቁስና ትጥቅ ለማማሏት ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ሰልጣኝ ታዳጊዎች ትምህርታቸውን ከስልጠናው በተጓዳኝ ለማካሄድ ከወላጆቻቸው ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ ስልጠናውን መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡

በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም የትምህርት ቤቶችን መዘጋት ተከትሎ ታዳጊዎቹ በስልጠና ያገኙት ብቃት የሚለካበት ውድድር እንደሚካሄድም ጠቁመዋል፡፡

የስልጠናው ዓላማ በቀጣይ አራት ዓመታት ኢትዮጵያን ከ20 ዓመት በታች በአፍሪካ የእግር ኳስ ዋንጫ ማሳተፍ እንደሆነ  አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል፡፡

ታዳጊ ወጣቶቹ ለዚህ ብቁ የሚያደርጋቸው የእግር ኳስ መሰረታዊ ጥበብና እውቀት እንዲጨብጡ ይዙ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌዴሪሽን ስራ አስፈጻሚና የሴቶች እግር ኳስ ልማት ሰብሳቢ ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙን ፤ ፕሮጀክቶች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህብረተሰቡ በተለይም ለእግር ኳስ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው ጠቁመው፣ የስፖርት አደረጃጀቶችን በማጠናከር የክልሉን ስፖርት እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል፡፡

በፕሮጀክት ታቅፈው ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙ ወጣቶች ስልጠናውን ከትምህርታቸው በተጓዳኝ  በመከታተል ሀገራቸውን እንዲያስጠሩም መክረዋል፡፡

የአሶሳ ፕሮጀክት የሴቶች አሰልጣኝ አሚና ማሞ ፤ ስልጠናው ላለፉት ወራት ሲካሄድ መቆየቱን ለኢዜአ ተናገራለች፡፡

የታዳጊዎቹ ስልጠና አቀባበል የሚበረታታ እንደሆነ ጠቁማ፣ድጋፉ በስልጠናው የሚገጥሟቸውን ችግሮች ያቃልለናል ብላለች፡፡

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምስጋናም አቅርባለች፡፡

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር በማሰልጠኛ ሜዳ ያለው ችግር እንዲፈታ ጠይቃለች፡፡

በፕሮጀክት ከታቀፉ ሰልጣኞች መካከል ታዳጊ ወጣት ቢልግራም ተፈራ በበኩሉ ፤በፕሮጀክት ታቅፎ እግር ኳስ ስልጠና በመሳተፍ ብቃት ያለው ተጫዋች መሆን ከልጅነቱ ጀምሮ ሲመኘው እንደቆየ ይናገራል።

የፕሮጀክቱ ተሳታፊ ደስተኛ መሆኑን የገለጸው ቢልግራም፤ስልጠናው በትምህርቱ ላይ ጫና እንዳልፈጠረበትም ገልጿል፡፡

በእግር ኳስ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስጠራት ራዕይ እንዳለውም አስታውቋል፡፡

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልሙኒዬም አብዱልዋሂድ በበኩላቸው፤  ሳላሃዲን ሰይድና ሌሎችንም የእግር ኳስ ስፖርተኞች ያፈራው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሁንም በርካታ ተሰጥኦ ያላቸው ተተኪ ወጣቶች ሊወጡበት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

አስተዳደሩ የስልጠና ሜዳ ደረጃ በማሻሻል እስከ መጪው ክረምት ወቅት ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ቃል ገብተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት በታዳጊዎች ደረጃ በተካሄዱ የእግር ኳስ ጨዋታዎች አበረታች ውጤት ማስመዝገቧ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም