በምስራቅ አፍሪካ ሽብርተኝነትና ህገ ወጥ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የቀጠናው አገራት በጋራ ይሰራሉ

461

ሚያዚያ 8/2014/ኢዜአ/  በምስራቅ አፍሪካ ሚስተዋለውን ሽብርተኝነትና ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የቀጠናው አገራት በጋራ የሚሰሩ መሆኑን የአገራቱ ወታደራዊ ሃላፊዎች ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሶማሊያና ጅቡቲ የሚሳተፉበት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ወታደራዊ የመረጃ ደህንነት ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በሽብርተኝነት፣ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ህገወጥ የሰዎች ንግድና እውቅና በሌለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ የማይጠፋበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ልዩ ትኩረት ያሻዋል ተብሏል፡፡

በቀጠናው አል ሸባብ፣ አይ ኤስ አይ ኤስ፣ ዳኤሽና ሌሎች ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች የሚንቀሳቀሱበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር 1991 ከዜያድ ባሬ መንግስት ውድቀት በኋላ የሽብር ቡድኖች ሶማሊያን የጉረቤት አገራትን ለማጥቃት እንደ መነሻ የተጠቀሙባት መሆኑን በኢፌዴሪ የመከላከያ የመረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ብርሃኑ በቀለ ይናገራሉ።

በ2007 በዩጋንዳና በሶማሊያ የደረሰው ተደጋጋሚ ጥቃት እንዲሁም በ2013 በኬንያ ሳውዝ ጌት የገበያ ማዕከል የደረሰውን የሽብር ጥቃት የዚሁ ምክንያት መሆኑን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያም አሸባሪዎቹ የህወሃትና የሸኔ ቡድኖች በተለያዩ አከባቢዎች በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ንጹሃን ዜጎችን የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡  

በመሆኑም በአንድ አገር የተከሰተ መልካምም ሆነ መጥፎ አጋጣሚ ዳፋው ለሌሎችም አገሮች የሚተርፍ በመሆኑ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ችግሩን ለመቆጣጠር በጋራ መቆም አለባቸው ብለዋል፡፡

ሽብርተኝነት፣ ህገወጥ የገንንዘብ ዝውውር፣ በሰዎች ላይ መነገድና ሌሎች ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች የቀጠናው ስጋት መሆናቸውን ገልጸው ችግሮችን ለመከላከል የጋራ ምቹ አጋጣሚዎችን መፍጠር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የጅቡቲ መከላከያ የመረጃ ደህንነት ሀላፊ ኮሎኔል ሜጀር አደን ደዋሌ፤ የመረጃ ደህንነት ማዕከል የማንኛውም ወታደራዊ ሀይል የጀርባ አጥንት መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

ሽብርተኝነትና ህገወጥነትን ለመቆጣጠር የሚደረገው ወታደራዊ ዘመቻ ያለ መረጃ ቅብብሎሽ ከግብ መድረስ አይችልም ብለዋል፡፡

ጅቡቲና ኢትዮጵያ በሚኒስትሮችና ወታደራዊ አዛዦች ደረጃ በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ገልጸው ወደ መረጃ ደህንነት መውረዱ ተግባራዊነቱን የበለጠ ያሳልጠዋል ብለዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ጸጥታ አደገኛ ደረጃ ላይ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር የተጀመረው ግንኙነት በሁሉም የቀጠናው አገሮች እውን እንዲሆን ጅቡቲ ቁርጠኛ ናት ብለዋል፡፡

የሶማሊያ ብሄራዊ መከላከያ ወታደራዊ መረጃ ደህንነት ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ሳኢድ ሞሀመድ ሳኢድ፤ የምስራቅ አፍሪካ ወታደራዊ መረጃ ደህንነት ፎረም በቀጠናው ያሉ የጸጥታ ስጋቶችን በጋራ ለመመከት ያግዛል ብለዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ አገራት የጋራ ጠላታችን የሆነውን ሽብርተኝነትና ህገ ወጥነት በጋራ ለመቆጣጠር ጠንካራ መረጃና የባህል ልውውጥ እንፈጥራለን ብለዋል፡፡

በዚህም የሽብርተኝነት እንቅስቃሴን በቀላሉ ለመቆጣጠርና ቀጠናውን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት ማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ አገራት ወታደራዊ የመረጃ ደህንነት ፎረም ተሳታፊዎች በቆይታቸው የአንድነት ፓርክን፣ የወዳጅነትና እንጦጦ ፓርክን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም