በአዲስ አበባ የትራፊክ ቁጥጥርን በማሻሻል የትራፊክ አደጋን የመቀነስ ስራ እየተከናወነ ነው

439

ሚያዚያ 8/2014/ኢዜአ/  የትራፊክ ቁጥጥርን በማሻሻል አደጋን የመከላከልና የመቀነስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጄንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በዛሬው እለት የገመገመ ሲሆን የትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎችን አዲስ የደንብ ልብስም ይፋ አድርጓል።   

የኤጄንሲው የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር እና ኩነት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ቢንያም ጌታቸው፤ የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ የተሳለጠ ለማድረግ በተለይም የትራፊክ ህግና ደንብን የማስከበር ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ጥብቅ የትራፊክ ቁጥጥር ስራዎችን ማድረግ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመተግበርና አሰራሮችን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራዎችም በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ከተቆጣጣሪዎች፣ ከአስተባባሪዎችና ከሱፐርቫይዘሮች ጋር በቀላሉ መረጃዎችን መለዋወጥ የሚያስችሉ አሰራሮች እየተተገበሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የትራፊክ ደንብን ተላልፈው የሚያመልጡ አሽከርካሪዎችን ተከታትሎ ለመያዝ 119 ተንቀሳቃሽ  ስልኮች በስራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል ዳይሬክተሩ።

የትራፊክ ፍሰት ችግር ባሉባቸው አካባቢዎች በፍጥነት ለመድረስ የሚያገለግሉ 70 የሞተር ብስክሌቶችም አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ አሁን ላይ ከ920 በላይ የትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎች መኖራቸውን ጠቁመው ለቁጥጥሩ የሚመች አዲስ የደንብ ልብስ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል።

በምህንድስናው ዘርፍ የሚከናወኑ ትግበራዎችና ማሻሻያዎችን ማድረግና በመንገድ ደህንነት ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑም ይገኛሉ።

ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 705 ሺህ 47 ደንብ ተላልፈው የተገኙ አሽከርካሪዎች በተለያየ ደረጃ መቅጣቱንም አስታውቋል።  

በብሉምበርግ ኢኒሺዬቲቭ የመንገድ ደህንነት የዳታ ባለሙያ ወይዘሮ ሜሮን ጌታቸው፤ በ2014 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት በትራፊክ አደጋ የሞት ምጣኔ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል።

በስድስት ወራት ብቻ በትራፊክ አደጋ የ215 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በተደረገው ጥናት መሰረት ከ5 የትራፊክ አደጋ የሞት ምክንያት አራቱ የሚደርሰው በእግረኞች ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም