በአገራችን እየገጠሙን ያሉትን ጊዜያዊ ችግሮች ለማለፍ ሁላችንም ልንተባበር፣ ልንተጋገዝና ልንረዳዳ ይገባል

85

ሚያዚያ 8/2014/ኢዜአ/  በአገራችን እየገጠሙን ያሉትን ጊዜያዊ ችግሮች ለማለፍ ሁላችንም ልንተባበር፣ ልንተጋገዝና ልንረዳዳ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር እንድሪስ ተናገሩ።

የታላቁን ረመዳን ወር ምክንያት በማድረግ ወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን ከኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጋር በመተባበር ከ500 በላይ አቅመ ደካሞችን አስፈጥሯል።

በኢፍጣር  መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ  ኡመር እድሪስ መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም በአገራችን እየገጠሙን ያሉትን ጊዜያዊ ችግሮች ለማለፍ ሁላችንም ልንተባበር፣ ልንተጋገዝና ልንረዳዳ ይገባል ነው ያሉት።

በተለይ ህዝበ ሙስሊሙ አሁን በታላቁ የረመዳን ወር ላይ የሚገኝ በመሆኑ መልካም ተግባራትን ተባብሮና ተጋግዞ መስራት አለበት ብለዋል።

የወንድም ካሊድ ተግባር ለዚህ አንድ ጥሩ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎችም ተመሳሳይ ተግባራትን በማከናወን ለተቸገሩ ሁሉ ሰብአዊነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

በኢፍጣር ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢትዮ- አንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ፤ አገሪቱ  በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ባለችበት በአሁኑ  ወቅት ይህን መሰል ስራዎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።

የወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን የተጎዱና ጎዳና ላይ የወደቁ ወገኖችን በማንሳት ድጋፍ በማድረግ ለሰብአዊነት መቆሙን በተግባር እያሳየ በመሆኑ ልናመሰግነው፣ ተግባሩን ልንደግፈውና ልናግዘው ይገባልም ነው ያሉት።

የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕም በጦርነቱ ለተፈናቀሉና በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን በመርዳትና በማገዝ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፤ ይህንንም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን መስራች ካሊድ ናስር፤ ፋውንዴሽኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ረመዳን ከገባ ጀምሮ አቅመ ደካሞችንና ችግረኞችን በማገዝ ላይ ይገኛል ብሏል።

የወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን ከተቋቋመ ጀምሮ ችግረኞችን በመርዳት፣ በማገዝና በርካታ ሰዎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት ስልጠናዎችን በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም