ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት የከተማ ግብርና ማስጀመሪያ መርሓ ግብር በገላን ከተማ ተካሄደ

91

ሚያዚያ 8/2014/ኢዜአ/ በብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ሴቶች ሊግ አስተባባሪነት ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት የከተማ ግብርና ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በገላን ከተማ ተካሄደ።

መርሓ ግብሩ "ምግቤን ከጓሮዬ" በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን በክልሉ 21 ዞኖች እና 19 ከተሞች ላይ የሚገኙ ሴቶች የሚሳተፉበት እንደሆነም ተገልጿል።

በገላን ከተማ በተካሄደው የማስጀመሪያ መርሓ ግብር ላይ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ሴት አደረጃጀት አመራሮችና የኦሮሚያ ብልጽግና ቅርንጫፍ ሴት አደረጃጀት አመራሮች ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ስራ አስፈፃሚ አባል ወይዘሮ ህይወት ሃይሉ እንዳሉት፤ ይህ መርሐ ግብር በአገር ደረጃ 6 ሚሊዮን ሴቶችን የማሳተፍ ዕቅድ ይዞ መጀመሩን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው መርሃ ግብርም የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸው፤ ሴቶች ምግባቸውን ከጓሮአቸው ለማግኘት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ሴቶች ሊግ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሱራኔ አለማየሁ በበኩላቸው፣ መርሃ ግብሩ በመላው ኦሮሚያ ያሉ ሴቶች የሚሳተፉበት ይሆናል ብለዋል።

በዚህም በክልሉ እስከ ሁለት ሚሊዮን ሴቶችን ለማሳተፍ መታቀዱን አንስተዋል።

የክልሉ ሴቶች በያሉበት ሆነው የከተማ ግብርናን በማከናወን የኑሮ ውድነት ጫናውን መቋቋም እንዲችሉ ጥሪ አቅርበዋል።

''በገላን በከተማ በውስን አከባቢዎች የተጀመረው መርሃ ግብር በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ይተገበራል'' ያሉት ደግሞ የከተማዋ ከንቲባ ወይዘሮ ወይንሸት ግዛው ናቸው።

የማስጀመሪያ መርሃ ግብሩም በግለሰብ መኖሪያ ግቢ፣ በትምህርት ቤቶች እንዲሁም በተለያዩ ክፍት ስፍራዎች አትክልት እና ፍራፍሬዎችን በመትከል እና በመጎብኘት ነው የተጀመረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም