የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት በተለያዩ የመፍትሄ አማራጮች እልባት እየተሰጠው ነው

275

ሚያዚያ 8/2014/ኢዜአ/  የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረትን ለማቃለልና ስርጭቱን ለማፋጠን በተለያዩ የመፍትሄ አማራጮች እልባት እየተሰጠው መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በ2014/15 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ ሚኒስቴሩ ከክልሎችና የፌደራል ባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ እየተወያየ ነው።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን፤ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት በዓለም በተፈጠሩ ክስተቶች እንዲሁም በውስጥና የውጭ ጫናዎች የግብርና ዘርፉ እየተፈተነ ይገኛል።

ለግብርና ምርታማነት አስፈላጊ የሆነው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት አንደኛው ችግር መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ለመፍታት በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የማዳበሪያ አቅርቦት አይኖርም በማለት የሀሰት መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት መኖራቸውን የጠቆሙት ዶክተር መለስ፤ እጥረቱን ለማቃለልና ስርጭቱን ለማፋጠን የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረትን ተከትሎ በአማራጭ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመተካት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

በመሆኑም የግብርናው ዘርፍ ተዋናይ ባለድርሻ አካላት፤ ግብርና የሕልውና ጉዳይ መሆኑን በቅጡ በመረዳት ሁሉም ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ግብርና አማራጭ የሌለው የኢትዮጵያ ክፍለ ኢኮኖሚ መሰረት በመሆኑ የትኛውንም አማራጭ በመጠቀም ያገጠመንን ፈተና ለመቋቋም በጋራ መስራት አለብን ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የማዳበሪያ ግብዓት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ በመሆኑ በአቅርቦትና ስርጭቱ የትራንስፖርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና ሌሎችም ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በምርት ዘመኑ ከሚያስፈልገው 19 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እስካሁን 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ግዥ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ መጓጓዙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም