በመረጃ ክልከላ፣ በመገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት ለመፍታት ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ሊገባ ነው

163

ሚያዝያ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) በመረጃ ክልከላ፣ በመገናኛ ብዙሃን እና ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት መፍታት የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ መንግስት መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን የምርመራ ስራዎች እና መረጃዎችን ተደራሽ እንዲያደርጉ ቁርጠኝነት ቢኖረውም የመረጃ ፍሰቱ ላይ ከትናንት የተረከብናቸው ከፍተኛ ችግሮች አሉ ብለዋል።

የስራ ሃላፊዎች እና ተቋማት በአብዛኛው ለቦታው አዲስ ነኝ፤አይመለከተኝም እና ሌሎች ምክንያት በማቅረብ ለመገናኛ ብዙሃኑ ተግበራት ማነቆ ይሆናሉ ነው ያሉት።

ይህን በአገሪቱ በስፋት የሚስተዋልን ችግር ለመቅረፍ የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ውይይት ተደርጎበት ለትግበራ ዝግጁ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

መመሪያው ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታችኛው የኮሙኒኬሽን እርከን የግንኙነት አሰራር የሚፈጥር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ የህዝብ ግንኙነት ባለሞያዎች ተቋማቸውን የሚያስተዋውቁበት እንዲሁም ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ያላቸው ግንኙነት የሚያጠናክሩበትን እድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የህዝብ ግንኙነት ባለሞያዎችን በስልጠናዎች የማገዝ፣ የአቅም ግንባታ ስራዎች እና ሌሎች ተግባራትም በቀጣይ በትኩረት የሚሰራባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ 

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም