የሀዋሳ ወጣቶች በተፈጠረላቸው የስራ እድል ህብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገለጹ

87

ሀዋሳ ሚያዚያ 5/2014 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን በተፈጠረላቸው የስራ እድል ራሳቸውን ጠቅመው ህብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገለጹ፡፡

ወጣቶቹ የመንግስት ቅጥርን ሳይሆን ጊዜው የሚፈልገውን ለመስራት ራስን ማዘጋጀት ይገባልም ብለዋል።

 የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ካደራጃቸውና የቦታ ርክክብ ካደረጉት ወጣቶች ለኢዜአ እንደተናገሩት አስተዳደሩ ባደረገላቸው እገዛ ራሳቸውንና ህብረተሰቡን ለመጥቀም ተዘጋጅተዋል።

ከወጣቶቹ መካከል በታቦር ክፍለ ከተማ ሆገኔ ዋጮ ቀበሌ ነዋሪዋ ወጣት ነፃነት ዶዮ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በስነ ህዝብ ጥናት የሙያ ዘርፍ ተመራቂ መሆኗ ትግልጻለች።

ወጣቷ አክላም የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር በአጭር ጊዜ የስራ እድል ተጠቃሚ ስላደረጋት ደስተኛ መሆኗንም ተናግራለች፡፡

ከጓደኞቿ ጋር በማህበር ተደራጅተው የመስሪያ ሼድ መረከባቸውን ገልጻ ወደ ስራ ለመግባት የወሰዱት ስልጠናም አነቃቂና የመንግስት ስራ ጠባቂ የነበረው አስተሳሰቧን  እንደቀየረው ገልጻለች።

በከተማ አስተዳደሩ የተሰጣት የስራ እድል ጥያቄዋን የመለሰ መሆኑን የተናገረችው ወጣቷ፣ ማህበረሰቡን በአግባቡ እንደምታገለግል ተናግራለች።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ታመነ ተመስጌን በበኩሉ በ2012 ዓ.ም  ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ማኔጅመንት ተመርቆ ያለስራ መቀመጡን ጋልጿል።

ከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸለት የሥራ እድል ተደራጅተው ስራ መጀመር የሚያስችላቸውን ስልጠና እና የመስሪያ ቦታ መረከባቸውን ተናግሯል።

ወጣቱ ለአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት መሆኑን ጠቅሶ፣ በተሰጠው እድል ተጠቅሞ ራሱንና ቤተሰብን መለወጥ በተለይም ከዩኒቨርሲቲ ለተመረቀ ወጣት ግዴታ ነው ብሏል።

ከተማ አስተዳደሩ በአጭር ጊዜ አደራጅቶ ፈጣን ምላሽ መስጠቱን ያደነቀችው ሌላኛዋ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተመረቀቸው ነፃነት አሸናፊ ናት።

ያለስራ የተቀመጠችበትን ጊዜ በሚያካክስ ሁኔታ ሰርታ ራሷንና አካባቢዋን ለመለወጥ እንደምትተጋም ገልጻለች።

ወጣቷ ተደራጅታ ለመስራት ባሰበችው የካፌና ሬስቶራንት ስራ በተመጣጣኝ ዋጋ ህብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀቷን ተናግራለች።

ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የተመረቀው ተመስገን ቡሹራ ለህብረተሰቡ አትክልትና ፍራፍሬ ለማከፋፈል ከጓደኞቹ ጋር ተደራጅተው  ከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጀላቸውን የመስሪያ ሼድ መረከቡን ጠቅሷል።

በቀጣይ በሚመቻችለት የገንብዘ ድጋፍ ተጠቅሞ ማህበረሰቡን በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡

እንደወጣቱ ገለጻ በዩኒቨርሲቲ ቆይታ ወቅት የመንግስት ቅጥርን ከማሰብ ሌሎችን አማራጮችን መመልከት የስራ አጥነቱን ለመቀነስ ስለሚያስችል አስተሳሰብን መቀየር ይገባል፡፡

የሃዋሳ ከተማ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ዳሪሞ ባለፉት ሁለት ወራት ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተመረቁ 1 ሺህ 683 ወጣቶች መለየታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም ውስጥ 1 ሺህ 10 የሚሆኑትን ወደ ስራ ለማስገባት በተፈጠረ የተግባቦት መድረክ የመንግስት ቅጥር የሚጠብቀውን ወጣት አመለካከት መቀየራቸውን ገልጸዋል።

"ወጣቶቹ በንግድና አገልግሎት፣ በከተማ ግብርና፣ በኮንስትራክሽንና በሌሎች ዘርፎች ለማሰማራት የመሬት አቅርቦት ልየታና የማልማት ስራ እየተከናወኑ ነው" ብለዋል፡፡

በቀጣይ ማህበራቱ ውጤታማ እንዲሆኑ ተከታታይ ስልጠናዎችን እንደሚሰጣቸው ገልጸው፤ ወደ ኢንዱስትሪ እስኪሸጋገሩ ድጋፍ እንደሚደረግ ኃላፊው አስታውቀዋል።

በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው በጀት ዓመት ለ25 ሺህ ወጣቶች ስራ ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም