በወልድያ ከተማ ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረው መንገድ ስራ መጋተት በነዋሪዎች ላይ ችግር ፈጥሯል

125

ደሴ (ኢዜአ) ሚያዚያ 7/2014 በወልድያ ከተማ ከአራት ዓመት በፊት ተጀምሮ የነበረው የሰባት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ መጓተት በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በበኩሉ መንገዱን ለመስራት ኮንትራት የወሰደው ሥራ ተቋራጭ የሥራ አፈጻጸሙ ደካማ በመሆኑ ውሉ እንዲቋረጥ መደረጉን ገልጿል።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ፈንታው መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው ከ4 ዓመት በፊት የሰባት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንግድ ሥራ ተጀምሮ ነበር።

የመንገዱ መገንባት የከተማውን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቀሴ ለማነቃቃት ፋይዳው የጎላ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

"ይሁንና የመንገዱ ግንባታ ከመዘግየቱ ባለፈ በአሁኑ ወቅት ሥራው በመቆሙ ግራ ገብቶናል፣ መንገዱ ባለመጠናቀቁም ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረግን ነው" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።

መንገዱ ሳይሰራ ተቆፍሮ መቅረቱና የውሃ መፋሰሻ ቦዮች በአግባቡ አለመሰራታቸው ህብረተሰቡን ለአካል ጉዳት ጭምር እያጋለጠ በመሆኑ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

መንገዱ ባለመሰራቱ እንደልብ ወጥቶ ለመግባት ከመቸገራቸው ባለፈ በቤታቸው ውስጥ አቧራ እየገባ ከነቤተሰባቸው ለጤና ችግር እያጋለጣቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ ሻምበል ባየ ዓለሙ በበኩላቸው በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረው መንገድ እስካሁን መጓተቱ ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ገልጸዋል።

"መንገዱ ተቆፍሮ ሳይሰራ በመቅረቱ በአሁኑ ወቅት የቆሻሻ መጣያ ጭምር እየሆነ ከተማውን ከማቆሽሽ ባለፈ በጤናችን ላይ ችግር እየፈጠረ ነው" ብለዋል።

በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ የራሱን ጫና በመፍጠሩ ለተጨማሪ ችግር እየዳረጋቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

መንግስት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የተቋረጠው የመንገዱ ግንባታ ሥራ እንዲጀመርና ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ በማድረግ ችግራቸውን እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

የወልድያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲበ ዶክተር ዳዊት መለሰ በበኩላቸው፣ የመንገዱ መጓተት የመልካም አስተዳደር ችግር ከመፍጠሩ ባለፈ በከተማዋ እድገት ላይ ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል።

የተቋረጠው የግንባታ ሥራ እንዲቀጥል ከተማ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

"የግንባታ ሥራው ፈጥኖ እንዲጠናቅ ከተማ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው" ሲሉም ዶክተር ዳዊት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮምቦልቻ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሳምሶን ተስፋዬ በበኩላቸው፣ መንገዱን ከአራት ዓመት በፊት ለሥራ ተቋራጭ ተሰጥቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

"በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ በተደረገው ስምምነት መሰረት ግንባታው በአሁኑ ወቅት መጠናቀቅ ቢኖርበትም አፈጻጻሙ 46 በመቶ ላይ ነው" ብለዋል።

ኢንጂነር ሳምሶን እንዳሉት ለመንገዱ ግንባታ ሥራ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ወደ ሥራ ተገብታል።

"ይሁን እንጂ በተቋራጩ አቅም ውስንነትና አሸባሪው ህወሓት በለኮሰው ጦርነት ምክንያት ሥራው ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል" ብለዋል።

ይህም በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ በመፍጠሩ አስተዳደሩ ውሉን አቋርጦ ግንባታውን በራሱ በማከናወን ለማጠናቀቅ ውሳኔ ላይ መድረሱን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የግንባታ ስራውን በራስ አቅም ለመስራት የቅደመ ዝግጅት ሥራው መጠናቀቁን ገልጸው፣ እስከ ሦስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ መንገዱን ለማጠናቀቅ በቅንጀት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም