ህብረተሰቡ ህጻናትን ከፖሊዮ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ኢንስቲትዩቱ አሳሰበ

323

ባህር ዳር ፤ ሚያዚያ 7/2014(ኢዜአ) የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህጻናትን በማስከተብ ሃላፊነቱን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት አሳሰበ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ  የሚሰጠው ሁለተኛ ዙር  የፖሊዮ መከላከያ የክትባት ዘመቻ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል።

በባህር ዳር አካዳሚ ትምህርት ቤት በተጀመረው የክትባት መረሃ ግብር ላይ  የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ዓባይነህ እንደገለጹት፤  ሁለተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።

የፖሊዮ በሽታ የረጅም ጊዜ ጠባሳ ጥሎ ከማለፍ ባለፈ ለከፍተኛ ሕመም እንደሚዳርግ ጠቁመው፤ በሽታውን  ለመከላከል ህብረተሰቡ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህጻናትን ሊያስከትብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወላጆች ለክትባቱ ዘመቻ ስኬታማነት  ማገዝ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በአማራ ክልል ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ለ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ህጻናት ክትባት ለመስጠት መታቀዱን የገለጹት ደግሞ የክልሉ  ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ናቸው።

አቶ በላይ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በጦርነቱ ምክንያት የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ካልወሰዱት ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ዋግምኸራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖችና ደሴ ከተማ አስተዳደር ውጭ ባሉ ሁሉም አካባቢዎች ሁለተኛው ዙር ክትባት ይሰጣል።

ክትባቱ የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካና በፖሊዮ በሽታ የሚመጣውን ጠባሳ አስቀድሞ ለመከላከል ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪ አቶ ፋሲል ታየ በበኩላቸው፤"ህብረተሰቡን የፖሊዮ ክትባት ባለመውሰድ ከሚከሰተው የልጅነት ልምሻ ለመታደግ የሃይማኖት አባቶች ለተከታዮቻቸው ትምህርት መስጠት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

በክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የጤናው ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም  የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም