ኢትዮጵያ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ሰላምን የማምጣት ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

370

ሚያዚያ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ሰላም ለማምጣት እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ፍሬያማ እንዲሆን ጽኑ ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው በተወያዩበት ወቅት መንግስት ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መንግስት እስረኞችን በመፍታት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳትና የብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድ ለማድረግ እያደረገ ያለው ዝግጅት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ መንግስት ያወጀው የተናጥል የሰብአዊ ተኩስ አቁም ወደ ክልሉ “ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት” እንዲኖር በር መክፈቱን ገልጸዋል።

ወደ መቀሌ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ በየጊዜው ከሚካሄዱ የአየር በረራዎች በተጨማሪ በዓለም የምግብ ፕሮግራም የተመራ የሰብአዊ እርዳታና የነዳጅ ቦቴዎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች በየብስ ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ እያጓጓዙ እንደሆነም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ሰላም ለማምጣት እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ፍሬያማ እንዲሆን ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ማመልከታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ጠቁሟል።

የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ጥረት በማድነቅ እየተደረገ ያለው ጥረት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ያመጣል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ መናገራቸውንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ሰላምን ለማምጣት እያደረጉት ያለውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባ መግለጻቸውም ነው የተነገረው።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አድርገው መሾማቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም