አገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ይካሄዳል

173

አዲስ አበባ  ሚያዝያ 7/2014  /ኢዜአ/ አገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው። 

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከሚያዚያ 9 እስከ 15/2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ጀሞ አካባቢ በሚገኘው የኢንተርፕራይዞች የምርት ማሳያና መሸጫ ማዕከል ይካሄዳል።

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ 181 ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም አስር አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል።

ከተሳታፊዎቹ 50 በመቶ የሚሆኑት ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪዎች በሴቶች የተያዙ ሲሆን በአካል ጉዳተኞች የተያዙ አምስት ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውም ተጠቁሟል።

ተሳታፊዎች በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በምርት ዲዛይን፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና በሌሎች ተያያዥ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ መሆናቸውም እንዲሁ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ አቦዘነች ነጋሽ እንደገለጹት፤ የኤግዚቢሽንና ባዛሩ ዋና አላማ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በምርት ጥራት ደረጃ የደረሱበትን ሁኔታ ለኅብረተሰቡ ለማስተዋወቅ ነው።

ተሳታፊዎች በአንድ ማዕከል እንዲገናኙና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እንዲሁም የገበያ ትስስር እንዲሳለጥ ማድረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኅብረተሰቡ በአገር በቀል ኢንተርፕራይዞች የሚቀርቡ ምርቶችን ገዝቶ በመጠቀም ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እድገት ያለውን አጋርነት እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከ20 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል፤ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የገበያ ትስስር ይፈጥራል ተብሎም ግምት ተሰጥቶታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም