ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቡና ወጪ ንግድ ከ894 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

482

ሚያዝያ 7 2014 (ኢዜአ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቡና ወጪ ንግድ ከ894 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ባለስልጣኑ ከቡና ምርት ጀምሮ እስከ ኤክስፖርት ድረስ የተቀናጀ የቁጥጥር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በተያዘው ዓመት ከ210 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ መላኩን ገልፀው፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር  የ43 ነጥብ 66 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ተናግረዋል።

በዚህም  ከ894 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መገኘቱንና ገቢው ከተያዘው እቅድ አንጻር 133 በመቶ አፈጻጸም እንደተመዘገበበት ገልፀዋል።

ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 74 ነጥብ 52 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ተናግረው የምርት ጥራትን ማሳደግ፣ ግብይትን ማዘመን እና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስርዓቶች መዘርጋታቸው ለእቅዱ መሳካት ወሳኝ ሚና ማበርከታቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ባለስልጣኑ የቁጥጥር ስርአቱን የሚመራበት ሶፍት ዌር በማበልጸግ ገቢራዊ ማድረጉም ለእቅዱ ስኬት ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም የገለጹት ሃላፊው በቀጣይ ገቢውን ወደ ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ እንደሚተጋም ጠቁመዋል።

በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ እና በመጋዘን ተከማችተው በተገኙ እንዲሁም የምርት ግብይት በተላለፉ አካላት ላይ በተወሰደ እርምጃ ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ መደረጉንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም