በአፋር ክልል በሠሙሮቢ-ገለአሎ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ለተጎዱ ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው

174

ሠመራ፤ ሚያዚያ 7/2014(ኢዜአ) በአፋር ክልል ሠሙሮቢ-ገለአሎ ወረዳ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ።

ድጋፉ እየተደረገ ያለው በተከሰተው  የእሳት አደጋ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ከ400 በላይ ወገኖች መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አቶ ሀሰን ሃንዴ ለኢዜአ ገልጸዋል።


ከክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለተጎጂዎች ሰብአዊ ድጋፍ እያቀረበ ይገኛል ያሉት የወረዳው አስተዳዳሪ አልባሳት ፣ የተለያዩ ምግብ-ነክ ቁሳቁሶችና ምንጣፎች ለተጎጂ ወገኖች እየተከፋፈሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከአጎራባቹ  አማራ ክልል የቀወት ወረዳ ህዝብና አመራሮችም  ለተጎጂዎቹ   ከ100ሺህ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

ተጎጂዎቹ በአደጋው ለዘመናት ያፈሩት ንብረት ሙሉ በሙሉ የወደመባቸው በመሆኑ መንግስት  ከሚያደርገው ድጋፍ  በተጓዳኝ የሌሎችም  የህብረተሰብ ክፍሎች ወገናዊ እገዛ  እንደሚያስፈልግ ነው አቶ ሀሰን የገለጹት።

ድጋፍ ከተደረገላቸው  መካከል አቶ አብዱ መሐመድ በሰጡት አስተያየት፤ በአደጋው  ቤትና ንብረታቸው እንደተቃጠለባቸው ተናግረዋል።

የተወሰኑ ምግብና  አልባሳት ድጋፍ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው አመልክተዋል።

ወይዘሮ ፋጡማ ሙሳ በበኩላቸው፤  በአደጋው ሙሉ ንብረታቸው መውደሙን ጠቅሰው፤ በመንግስት በኩል ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።


ይህም ሆኖ በተለይም የአልባሳትና የምግብ ማብሰያ ችግር ያለባቸው በመሆኑ መንግስትና ሌሎችም በጎ አድራጊዎች መደገፋቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም