የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን የ80 ዓመት ጉዞ የሚያሳይ ዓውደ ርዕይ ነገ በሀዋሳ ይከፈታል

208

ሀዋሳ ፤ ሚያዝያ 6/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) የተመሰረተበት 80ኛ ዓመት በማስመልከት የተዘጋጀ የፎቶና ቪዲዮ ዓውደ ርዕይ በደቡብና ሲዳማ ክልሎች ደረጃ ነገ በሀዋሳ ከተማ ይከፈታል።

ዓውደ ርዕዩ ኢዜአ ላለፉት 80 ዓመታት በሀገር ግንባታ ሂደት የነበረውን ሚናና  እስከ ዛሬ የተጓዘበት መንገድ የሚያመላክት መሆኑን የኢዜአ የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ ወንድይራድ ተናግረዋል።

የሲዳማና ደቡብ ክልሎች ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ዓውደ ርዕዩ ነገ  በሀዋሳ ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚከፈት አስታውቀዋል።

ዓውደ ርዕዩ   ለሶስት ቀናት ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ የተመለከተ ሲሆን፤ በተጨማሪም ኢዜአ ባለፈባቸው ዓመታት አስተማማኝ የዜና ምንጭ በመሆን መረጃ ለመገናኛ ብዙሃን  በማቀበል የነበረውና በቀጣይ በሚኖረው ሚና ላይ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

ቀደም ሲልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በተገኙበት በዋናው መስሪያ ቤት፤ ቀጥሎም በአዳማና ባህርዳር  ከተሞች በተመሳሳይ ዝግጅቶች ኢዜአ የተመሰረተበት 80ኛ ዓመት መከበሩን በወቅቱ ተገልጿል።